የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ -ለቀጣናዊ ሰላም - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ -ለቀጣናዊ ሰላም
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ማንን ነው የሚጎዳው? ማንንም! ይልቁኑ ለቀጠናው እና ለአለም የንግድ እንቅስቃሴ መረጋጋትን ለመፍጠር የኢትዮጵያ ወደ ባሕር በር መቅረብ ትልቅ ዋስትና ነው። እንዴት እንደሆነ ጉዳዩን በዝርዝር እንመልከት።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ በአፍሪካ ቀንድና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኗል። አያሌ የታሪክ፣ የሕግና የጂኦፖለቲካ ተንታኞች እንደሚስማሙበት፣ የኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት ማንንም ሀገር የሚጎዳ ወይም የሌሎችን ሉዓላዊነት የሚነካ አይደለም።
ይልቁንም ለቀጣናው ሰላም፣ ለቀይ ባሕር አካባቢ መረጋጋትና ለዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ ዋስትና የሚሰጥ ተፈጥሯዊና ምክንያታዊ ጥያቄ ነው።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላትና በዓለም ላይ በሕዝብ ብዛት ትልቋ የባሕር በር አልባ (Landlocked) ሀገር ናት።
እጅግ ፈጣን የሆነ እድገት ላይ ያለችው ይህች ሀገር የባሕር በር ማግኘቷ የህልውናና የረጅም ጊዜ ዕድገት ጉዳይ የሆነበት በርካታ ምክንያቶች አሉ።
ኢትዮጵያ ለውጭ ንግድ እንቅስቃሴዋ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮችን ለወደብ አገልግሎት ክፍያ ታወጣለች። ይህ ከፍተኛ ሀብት ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለግብርናና ለመሠረተ-ልማት ግንባታ ሊውል የሚችል በመሆኑ በሀገሪቷ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ትልቅ ጫና መፍጠሩ እሙን ነው።
በተለይ ለወደብ ኪራይ ከሚወጣው ከፍተኛ ወጪ ባለፈ፤ በአንድ ወይም በሁለት የጎረቤት ሀገራት ወደቦች ላይ ብቻ ሙሉ በሙሉ ጥገኛ መሆን የሀገሪቷን የንግድ እንቅስቃሴና የኢኮኖሚ ደህንነት ለከፍተኛ ሥጋት ይዳርጋል። በጎረቤት ሀገራት ዘንድ የሚፈጠር ማንኛውም አለመረጋጋት ወይም የፖሊሲ ለውጥ የኢትዮጵያን ሙሉ የንግድ እንቅስቃሴ በአንድ ጀምበር የማደናቀፍ አቅም አለው።
ኢትዮጵያ በያዘችው የእድገት ፍጥነት የምትቀጥል ከሆነ ደግሞ በቀጣዮቹ አሥርት ዓመታት ብቻ የሕዝቧ ቁጥር እና የኢንዱስትሪ ምርቷ እየጨመረ ሲሄድ፤ አሁን ያሉት የሎጂስቲክስ መስመሮች የምርት ፍሰቱን መሸከም አይችሉም።
ስለዚህ የራሷ የሆነ ዘላቂና አስተማማኝ የባሕር በር ማግኘት የቀጣይ ትውልድ ህልውናን የማረጋገጥ ጉዳይ ነው።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ስታነሳ አዲስ መሬት ለመውረር ወይም ባዶ ምኞት ለመሰንዘር ሳይሆን፣ በታሪክና በሕግ አሠራር የተደገፈ መሠረት ስላላት ነው። ኢትዮጵያ ለዘመናት የራሷ የባሕር በሮች ባለቤት እንደነበረች ዓለም ያወቀው እውነት ነው።
ከዓመታት በፊት በሀገሪቷ የነበረው የሽግግር መንግሥት ዋና ዓላማ ሀገሪቱን ወደ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ማሸጋገር እንጂ፣ የሀገርን የሉዓላዊነት ወሰን የሚያስከልሉና የባሕር በርን የመሰሉ ወሳኝ ሀገራዊ ሀብቶችን አሳልፎ የመስጠት ሙሉ የሕግና የሕዝብ ውክልና አልነበረውም።
ሆኖም የሕጋዊ ውክልና ክፍተት ባለበት ሁኔታ በ1980ዎቹ ማጠቃለያና በ1990ዎቹ መጀመሪያ ኢትዮጵያ የባሕር በር አልባ እንድትሆን ተደርጋለች።
በሕግና በዓለም አቀፍ አሠራር መሠረት የሀገር ስትራቴጂክ ሀብቶችን አጠቃቀምና ወሰን የሚወሰኑ ጉዳዮች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም በይፋዊ የሕዝበ-ውሳኔ መካሄድ ነበረባቸው። የሽግግር መንግሥቱ ወደቡን አሳልፎ ለመስጠት ያደረገው ውሳኔ በሕግ ፊት ውድቅና የሕዝብ ይሁንታ የሌለው በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ በሕገ-ወጥ መንገድ ያጣችውን ታሪካዊና ሕጋዊ መብቷን ብትጠይቅ ምክንያታዊና ትክክለኛ ያደርገዋል።
ወደ መጀመሪያው ጥያቄ እንመለስ፤ ለመሆኑ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ማንን ነው የሚጎዳው?
የኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት ለአፍሪካ ቀንድ ብቻ ሳይሆን ለቀይ ባሕርና ለዓለም አቀፍ የንግድ መስመር መረጋጋት ትልቅ አዎንታዊ ሚና ይጫወታል።
ለቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስር ማለትም ለጋራ ልማትና ኢንቨስትመንት፣ ለኤሌክትሪክና ንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ ለጋራ ብልፅግና ጠቃሚ ነው።
በተጨማሪም ቀይ ባሕርና የፋርስ ባሕረ-ሰላጤ የዓለም አቀፍ ንግድና የኃይል አቅርቦት ቁልፍ ማስተላለፊያዎች ናቸው። በአሁኑ ወቅት በዚህ ቀጣና የሚታዩት የባሕር ላይ የኮንትሮባንድ ንግድ፣ የባሕር ላይ ዘረፋ እና የፅንፈኛ ቡድኖች እንቅስቃሴ ለዓለም ንግድ ትልቅ ሥጋት ሆነዋል።
ኢትዮጵያ ጠንካራ የመከላከያና የባሕር ኃይል አቅም ያላት ሀገር በመሆኗ፣ ወደ ባሕር በር መጠጋቷ የዓለም አቀፍ የንግድ መርከቦች የሚያልፉበትን የኤደን ባሕረ-ሰላጤና የቀይ ባሕር መስመር አስተማማኝ ደህንነት ለመጠበቅ ያስችላል።
ሀገሪቷ በሰላም ማስከበር ያላትን የካበተ ልምድ በመጠቀም ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጋር በመተባበር የቀጣናውን ፀጥታና መረጋጋት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስጠበቅ ትልቅ አቅም ትሆናለች።
በአጠቃላይ፣ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የሌሎችን ሀገራት ጥቅም ወይም ሉዓላዊነት የሚጋፋ ሳይሆን፣ የታሪክና የሕግ እውነታዎችን ያገናዘበ፣ የሕዝቧን የህልውናና የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያረጋግጥ፣ እንዲሁም ለአፍሪካ ቀንድና ለዓለም አቀፍ ንግድ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት መሠረት የሚጥል ምክንያታዊ ጥያቄ ነው።
ይህንን ጥያቄ በዲፕሎማሲያዊ፣ በሰላማዊና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ መፍታት የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ቀጣናው ሀገራትና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የጋራ ጥቅም ነው።