ማዕከሉ የሚያወጣቸው አዳዲስ የሰብል ዝርያዎች የአርሶ አደሮች ምርታማነት እንዲጨምር አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ማዕከሉ የሚያወጣቸው አዳዲስ የሰብል ዝርያዎች የአርሶ አደሮች ምርታማነት እንዲጨምር አድርጓል
አሶሳ፤ጥቅምት 5/2019 (ኢዜአ)፦ የአሶሳ ግብርና ምርምር ማዕከል የሚያወጣቸው አዳዲስ የሰብል ዝርያዎች ምርታማነታቸውን በመጨመር ተጠቃሚነታቸውን እያሳደገው መሆኑን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኩርሙክ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ።
የአሶሳ ግብርና ምርምር ማዕከል በኩርሙክ ወረዳ አጉቤላ ቀበሌ 12 አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም እርሻ በ15 ሄክታር ማሳ ላይ እያለሙት የሚገኘውን በምርምር የተገኘ የሰሊጥ ሰብል የመስክ ጉብኝት አካሄዷል።
በወቅቱም አርሶ አደሮቹ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ማዕከሉ የሚያወጣቸው አዳዲስ የሰብል ዝርያዎች ምርታማነታችንን በመጨመር ተጠቃሚነታችንን እያሳደጉ ነው።
አርሶ አደር መብሩክ ሃሚስ፤ ከዚህ ቀደም በወረዳው በብዛት የሚታወቁት የሰብል ዓይነቶች በቆሎ እና ማሽላ እንደነበሩ አስታውሰው፣ አሁን ላይ ግን ማዕከሉ በሚያቀርባቸው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች አማካኝነት የሰሊጥ ሰብል እያለሙ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
እያለሙት የሚገኘው የሰሊጥ ሰብል ቁመና በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝና ከምርምር ማዕከሉ ጋር በመተባበር አስፈላጊውን ግብዓት እንዲያገኝ መደረጉንም ገልጸዋል።
ሌላው በእርሻ ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩት አቶ ኢብራሂም አወድ በበኩላቸው፤ ለአካባቢው ሥነ ምሕዳር ተስማሚ የሆኑ የሰብል ዝርያዎችን በመለየት ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።
ለሙከራ እያለሙት የሚገኘው የሰሊጥ ሰብል ጥሩ ገቢ የሚያስገኝ እና የአካባቢውን አርሶ አደሮች እያነቃቃ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
በተጨማሪም ማዕከሉ እና የግብርናው ዘርፍ አመራሮች በማሳው ላይ በየጊዜው በመገኘት ክትትልና ቁጥጥር እያደረጉ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የአሶሳ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አረሺድ አጠይብ በበኩላቸው፤ በዞኑ በኩታ ገጠም እና ቴክኖሎጂን በመጠቀም የግብርና ሥራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
እስካሁን በዞኑ ከ800 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በሰብል መሸፈኑን ገልጸው፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አርሶ አደሩ የቅባት እህሎችን በማልማት ተጠቃሚ እየሆነ እንደመጣም አመልክተዋል።
በኩርሙክ ወረዳ የሰሊጥ ሰብልን እያለሙ የሚገኙ አርሶ አደሮች ዘመናዊ ግብርናን የተረዱ እና ለሌሎች አርሶ አደሮች ተሞክሮ የሚሆን ውጤታማ የግብርና ሥራ እያከናወኑ እንደሚገኝ መመልከታቸውንም ተናግረዋል።
የአሶሳ ግብርና ምርምር ማዕከል በክልሉ በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ላይ የምርምር ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የተናገሩት ደግሞ በማዕከሉ የግብርና ኤክስቴንሽን ተመራማሪ ፍቃዱ ቤኛ ናቸው።
ማዕከሉ በኩርሙክ ወረዳ በምርምር የተገኙ የማሽላ እና የሰሊጥ ሰብሎችን አርሶ አደሩ እንዲያለማ በማድረግ፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት እያገዘ መሆኑንም አብራርተዋል።