በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ካለፈው ዓመት በእጥፍ ብልጫ ያለው ገቢ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ካለፈው ዓመት በእጥፍ ብልጫ ያለው ገቢ ተሰበሰበ
ሆሳዕና፤ጥቅምት 5/2019 (ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ካለፈው ዓመት በእጥፍ ብልጫ ያለው ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ገለፀ።
በክልሉ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ሰባት ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉም ተገልጿል።
የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ቀመሪያ ረሻድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በተያዘው በጀት ዓመት ከመደበኛና ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት 35 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ የሚያስችል ግብ ተጥሎ ወደ ተግባር ተገብቷል።
በቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ለገቢው ስኬታማነት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተግባቦት መፈጠሩን ጠቁመዋል።
ወጪን በራስ አቅም ለመሸፈንና የሕዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ክልሉ የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ መሰብሰብ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዚህም በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለመሰብሰብ ከታቀደው 8 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ውስጥ 7 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል።
የተሰበሰበው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ መጨመሩን ጠቁመዋል።
ግብር ከፋዩ ወቅቱን ጠብቆ በጊዜ የመክፈል ልምድ ማደጉ እና የገቢ አሰባሰብ ሂደቱን በቴክኖሎጂ የታገዘ ማድረግ መቻሉ ለገቢው መጨመር ዋና ዋና ምክንያቶች መሆናቸውን የተናገሩት ኃላፊዋ፤ ይህም ሥራ በቀጣይ ወራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በሆሳዕና ከተማ የደረጃ "ሀ" ግብር ከፋይ የሆኑት አቶ አዲሱዓለም መላዕክ ገቢያቸውን አሳውቀው የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱ እንደሚከፍሉ ገልጸዋል።
የልማት ሥራዎች የሚከናወኑት ግብር ከፋዩ ማኅበረሰብ የሚጠበቅበትን ግብር በወቅቱ መክፈል ሲችል በመሆኑ፣ ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በከተማው ሌላኛው ግብር ከፋይ አቶ አለማየሁ ተረፈ በበኩላቸው፤ ግብርን በወቅቱና በታማኝነት መክፈል ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሚጠቅሙ እንደ መንገድ፣ የትምህርትና የጤና ተቋማት ያሉ መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።
የግብር አከፋፈል ስርዓቱ እየዘመነ በመምጣቱ ያለምንም እንግልት የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱ በመክፈል ንግድ ፈቃዳቸውን አድሰው በመሥራት ላይ እንደሚገኙም አስረድተዋል።