ቀጥታ፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር ስራው ባሻገር በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ ነው

ሐረር፤ጥቅምት 5/2019 (ኢዜአ)፦ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር ስራው ባሻገር በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶችና በምርምር ስራዎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን አጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት  ጀማል ዩስፍ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ ዩኒቨርሲቲው በ2019 የትምህርት ዘመን ወደ ራስ-ገዝነት ለመሸጋገር በርካታ ስራዎች የሚሰራበት ዓመት ነው።

ለዚሁ ሽግግር የሚረዱ አስፈላጊ መመሪያዎችም ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር ባለሙያዎች እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር ተገምግመው ተዘጋጅተዋል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከመደበኛው የመማር ማስተማር ስራው በተጓዳኝ በምርምርና በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶች ማህበረሰቡንና አርሶ አደሩን  ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ የሚያከናውናቸውን ተግባራት በማጠናከር፣ የአካባቢውን ህብረተሰብ በላቀ ደረጃ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን ትኩረት ሰጥቶ እንደሚተገብር ፕሬዝዳንቱ አብራርተዋል።

በተለይም ችግር ፈቺ የሆኑ እንዲሁም የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጡ የሰብል፣ የአዝዕርትና የእንስሳት ምርምር ውጤቶችን ወደ ተግባር ለመቀየር በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው በአካባቢ ጥበቃ፣ በማህበረሰብ ጤና እና በሌሎች ዘርፎች ከአገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ አጋር ተቋማት ጋር ያለውን ትብብርና ትስስር በማጠናከር የምርምር ስራዎቹን እንደሚያጎለብት ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲው በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤና እና በሌሎች የሚያከናውናቸውን የማህበረሰብ አገልግሎት ተግባራት እንደሚያጎለብትም ዶክተር ጀማል አንስተዋል።

በተለይም ከነጻ የህግ አገልግሎት ተግባራት ጋር በተያያዘ ዩኒቨርሲቲው የሚያከናውነውን የማህበረሰብ አገልግሎት አጎልብቶ እንደሚቀጥል ጠቁመው፤ የመምህራን ልማት ማሳደግ ላይም አተኩሮ የሚሰራውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በመማር ማስተማሩ ረገድ  ዩኒቨርሲቲው በዘንድሮ የትምህርት ዘመን 5ሺህ የሚጠጉ አዳዲስ ተማሪዎችን ከዛሬ ጀምሮ እንደሚቀበል ጠቁመው፤ ለቅበላውም አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም