የጣና ፎረም እንግዶችን በተሟላ መልኩ ለማስተናገድ ተዘጋጅተናል - ኢዜአ አማርኛ
የጣና ፎረም እንግዶችን በተሟላ መልኩ ለማስተናገድ ተዘጋጅተናል
ባህርዳር፤ጥቅምት 5/2019 (ኢዜአ)፦ የጣና ፎረምን ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን በተገቢው መንገድ ለማስተናገድ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን በከተማዋ የሚገኙ ሪዞርትና ሆቴሎች አስታወቁ።
12ኛው የጣና ፎረም በባህር ዳር ከተማ ከጥቅምት 13 እስከ 15/2019 ዓ.ም ይካሄዳል።
ኢዜአ በባሕርዳር ከተማ ፎረሙን ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ የተደረጉ ዝግጅቶችን አስመልክቶ ከተለያዩ ሆቴሎች ኃላፊዎች ጋር ቆይታ አድርጓል።
በዘንድሮው የጣና ፎረም ለመታደም የሚመጡ የአህጉሪቱ መሪዎችና ሌሎች እንግዶች በሚፈለገው መልክ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ነው ኃላፊዎቹ የሚናገሩት።
የፈለገ ጊዮን ሪዞርት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አይችሉህም ወንድወሰን እንደገለጹት፤ በዘንድሮው የጣና ፎረም ለመሳተፍ የሚመጡ እንግዶች ምቾት ተሰምቷቸው እንዲመለሱ የሚያደርግ ዝግጅት አድርገናል።
በተለይ ደረጃውን የጠበቀ የእንግዳ ማረፊያና መመገቢያ ክፍሎችን፣ ሬስቶራንቶችንና የኢንተርኔት አገልግሎቶችን ከማሟላት ባለፈ የሄሊኮፕተር ማረፊያ ቦታዎችንም ጭምር ዝግጁ ለማድረግ መቻሉን ነው የገለጹት።
እንግዶች ከስብሰባ ውጭ ባላቸው ጊዜም በጣና ሃይቅና በአባይ ወንዝ ላይ እንዲዝናኑ ደሴቶችንና ገዳማትን እንዲጎበኙ ዘመናዊና ፈጣን ጀልባዎች መዘጋጀታቸውንም ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም በሪዞርቱ መስተንግዶ የሚሰጡ ባለሙያዎችን በማሰልጠንና በመመደብ፣ በከተማዋ ያሉ የመስሕብ ስፍራዎችን እንዲጎበኙና ጥሩ ጊዜ እንዲኖራቸው ለማድረግ ለረጅም ጊዜ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
በመሆኑም እንግዶችን በኢትዮጵያዊ እንግዳ ተቀባይነት መንፈስ በማስተናገድ ከከተማዋ አልፎ ለሀገር ገጽታ ግንባታ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማድረግ ተዘጋጅተናል ነው ያሉት።
የብሉ ናይል ሪዞርት እና ሆቴል የእንግዳ መቀበያ ክፍል ሱፐርቫይዘር አቶ ጌታቸው ይስማው፤ ለፎረሙ የሚመጡ እንግዶችን በተገቢው መንገድ ለማስተናገድ ለሆቴሉ ሰራተኞች ስልጠና በመስጠት እየተጠባበቅን ነው ብለዋል።
በተጨማሪም አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን በማሟላት፣መሰብሰቢያ አዳራሾችና መዝናኛ ቦታዎች የተሟሉና ምቾት የሚሰጡ እንዲሆኑ ለማድረግም ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።
እንግዶቹ የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ ለማድረግም የተጠናከረ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ሁለንተናዊ ዝግጅት አድርገናል ነው የሚሉት።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጋሻው እንዳለው በበኩላቸው፤ የጣና ፎረምን በስኬት ለማጠናቀቅ የተለያዩ ኮሚቴዎች ተዋቅረው እየተሰራ መሆኑን የገለጹ ሲሆን ከዚህ ውስጥም ሆቴሎች ይገኙበታል ብለዋል።
በተለይ እንግዶች የቆይታ ጊዜያቸውን አራዝመው የጣና ሃይቅን፣ የአባይ ወንዝና ሌሎችንም የመስህብ ሃብቶች እንዲጎበኙ ከሆቴሎች ፣ከሪዞርቶችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ተሰርቷል ነው ያሉት።