ኢትዮጵያ-በመደመር እሳቤ ነገዋን እየገነባች ያለች ሀገር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ-በመደመር እሳቤ ነገዋን እየገነባች ያለች ሀገር
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የምትከተለው የመደመር እሳቤ ሀገራዊ አቅምን አቀናጅቶና አስተባብሮ ወደ ላቀ የብልፅግና ምዕራፍ መሻገርን ግቡ ያደረገ ሀገር በቀል የሥልጣኔ ፍልስፍና ነው።
እሳቤው ያለፉትን ትውልዶች ስኬት በማክበርና ድክመቶችን በዕውቀት ላይ ተመስርቶ በማረም፣የሀገሪቱን የነገ ጉዞ በጸና መሰረት ላይ ለማቆም ያለመ ነው።
ይህ አይነቱ አካሄድ ሀገሪቱ በውስጣዊ አቅሟ ላይ በመተማመንና ሉዓላዊነቷን በማስጠበቅ፣ በፈጣን የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዕድገት ጎዳና ላይ እንድትራመድ የሚያስችል አስተማማኝ ሁኔታ ፈጥሯል።
የዚህ ፍልስፍና ግንባር ቀደም ማሳያ የሀገሪቱን ገፅታ የቀየሩትና በዓለም አቀፍ ደረጃ አድናቆትን ያተረፉት ግዙፍ ሜጋ ፕሮጀክቶች ናቸው።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ፣ የስንዴ ልማት ስኬት እንዲሁም በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች የተተከሉበት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የመደመር እሳቤ በተግባር የታየባቸው የታሪክ ምዕራፎች ናቸው። እነዚህ ግዙፍ ስራዎች የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባለፈ፣የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና በራስ አቅም ማረጋገጥ እንደሚቻል በተጨባጭ አሳይተዋል።
ሌላው የመደመር እሳቤ ትልቅ ማረጋገጫ የከተሞችን ውበትና የህዝብን ተጠቃሚነት ያረጋገጡት የኮሪደር እና የቱሪዝም ልማት ስራዎች ናቸው።በአዲስ አበባና በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች የተከናወኑት የኮሪደር ልማት ስራዎች የከተሞችን ደረጃ ያሳደጉ ለዜጎች ምቹ የመኖሪያ አካባቢን የፈጠሩ ናቸው።
እንደ አንድነት፣ወዳጅነትና እንጦጦ ፓርኮች እንዲሁም የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮና የታሪክ ፀጋ ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ጥቅም መቀየር አስችለዋል።በዲፕሎማሲና በውጭ ግንኙነት ረገድ፣ የመደመር እሳቤ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ያስቀደመና በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ ስትራቴጂካዊ አካሄድን ይከተላል።
ዘላቂ ልማት እና እድገትን ለማረጋገጥ አስተማማኝ የባህር በር የማግኘት ጥያቄን ቅድሚያ በመስጠት፣የምስራቅ አፍሪካንና የመላው አህጉሪቱን የጋራ ብልፅግና የሚያረጋግጡ ድልድዮችን እየገነባ ይገኛል።
ፍልስፍናው ከሀገር ድንበር ተሻግሮ አፍሪካውያን አቅማቸውን አስተባብረው እንዲጠቀሙ እና በራስ የመተማመን መንፈሳቸውን እንዲያሳድጉና ከጥገኝነት እንዲወጡ የሚያስችል አዲስ እይታን ፈጥሯል።በአጠቃላይ የመደመር እሳቤ የኢትዮጵያን የወደፊት ዕጣ-ፈንታ ከተረጂነት እና ከጥገኝነት አስተሳሰብ በማላቀቅ በብልጽግና መሰረት ላይ የሚያስቀምጥ የሥልጣኔ ፍኖተ ካርታ ነው።
ሀገሪቱ በግብርናው ዘርፍ ካስመዘገበችው የስንዴ ምርታማነት ስኬት ጀምሮ የከተሞችን ገፅታ እስከቀየሩት ዘመናዊ የኮሪደር ልማት ስራዎች ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች እሳቤው ነገን በተግባር የመቅረጽ ከፍተኛ አቅም እንዳለው ያሳዩ ናቸው።
ይህ ስትራቴጂካዊ አካሄድ የሀገር ውስጥ አቅምን በማጠናከርና የአፍሪካን የጋራ ትስስር እና አብሮ መልማትን በማስቀደም፣የወደፊቷ ኢትዮጵያ በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ላይ ያላትን ተፅዕኖ ፈጣሪነት ይበልጥ ያጎለብታል።