ቀጥታ፡

በአፋር ክልል በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ችግር ለገጠማቸው ወገኖች የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እየተደረገ ነው

ሰመራ ጥቅምት 4/2019 (ኢዜአ) ፦በአፋር ክልል በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ችግር ለገጠማቸው ወገኖች የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እየተደረገ ነው።

ከአዳማ የእህል ማከማቻ ማዕከላዊ መጋዘን በመጀመሪያው ዙር የተጫነው ሰብዓዊ ድጋፍ በክልሉ የቅድሚያ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ወገኖች በመከፋፈል ላይ ይገኛል።

በዛሬው ዕለትም በቢዱ ወረዳ ጊሪፎ ቀበሌ ለበርካታ ወገኖች ተደራሽ የተደረገ ሲሆን ድጋፍ የተደረገላቸው ወገኖችም ምስጋና አቅርበዋል።


 

በተፈጥሮ መዛባት ምክንያት በአካባቢው በተከሰተው ድርቅ ለችግር መጋለጣቸውን የገለጹት ነዋሪዎቹ ድጋፍ ባስፈለገን ጊዜ ደርሶልናል ብለዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል ወይዘሮ መይረም አብዱ፤ የተደረገልን ድጋፍ ልጆቻችን እና አጠቃላይ ቤተሰቡ ላጋጠመን የምግብ እጥረት መፍትሄ የሚሆነን ነው ብለዋል።


 

መንግስት በአካባቢው ያጋጠመውን የተፈጥሮ አደጋ በመረዳት ፈጣን ምላሽና ድጋፍ በማድረጉ አመስግነዋል።

ሌላኛዋ የድጋፉ ተጠቃሚ ወይዘሮ አሲያ መሐመድ፤ በአካባቢው ያጋጠመውን ችግር መንግስት አውቆ አስፈላጊውን ድጋፍ ስላደረገልን እናመሰግናለን ብለዋል።

በመንግስት ድጋፍ ባይደረግላቸው እርሳቸውና ቤተሰባቸው የከፋ ችግር ላይ ይወድቁ እንደነበር ተናግረዋል።

በመሆኑም እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎችም የአካባቢው ነዋሪዎች የተደረገላቸው ድጋፍ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልጸዋል።


 

የአፋር ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የክምችት ጥራትና ቁጥጥሮ ቡድን መሪ አቶ መሐመድ አብደላ፤ በክልሉ የቅድሚያ ቅድሚያ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ድጋፍ እየተዳረሰ መሆኑን ተናግረዋል።

ክልሉ በራሱ አቅም ድጋፍ ለሚሹ አካባቢዎች የሰብአዊ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱንና አሁንም በማድረግ ላይ መሆኑን አንስተው ከኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር የተላከውንም የቅድሚያ ቅድሚያ ለሚሹ ወገኖች እየደረሰ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የቢዱ ወረዳ የአርሻና ተፈጥሮ ሃብት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ የሱፍ መሐመድ፤ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በአካባቢው የተከሰተው ድርቅ ነዋሪዎችን ለችግር መዳረጉን ገልጸዋል።

በመሆኑም መንግስት ያለውን ችግር በመረዳት የሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽ ማድረጉ ወቅታዊና አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም