ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፤ በጠንካራ ወታደራዊ አቅምና ዲሲፕሊን የታነጸው የአፍሪካ የሰላም ዘብ!!

ኢትዮጵያ ለትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ እና ታላቅ ርዕይ የሚመጥን የመከላከያ ሰራዊት ገንብታለች። ይህ የሀገር መከታ ሰራዊት በታጠቃቸው ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ብቻ ሳይሆን በተላበሰው ወታደራዊ ዲሲፕሊን ለዓለም ምሳሌ የሆነ ድል አድራጊ ሰራዊት መሆኑን አስመስክሯል። በማድረግ አቅሙም ጠላቶች ከሩቅ የሚሸሹት ሆኗል።

ኢትዮጵያ የአሸናፊዎች ምድር ናት። የአሸናፊነት ተምሳሌትም ጭምር። የኢትዮጵያ የአሸናፊ ምድርነት እና ምሳሌነት ሁነኛው ማሳያ ደግሞ የሀገር መከላከያ ሰራዊቷ ጀግንነት የሚቀዳ ነው። ሰራዊቱ የቅድመ አያቶቹና አያቶቹን የድል አድራጊነት መንፈስ ከነሙሉ ክብሩ በትውልድ ቅብብሎሽ የተረከበ ብቻ ሳይሆን ያስቀጠለ የድል ፋና ወጊ ሰራዊት ነው።

ይህን የአሸናፊነት ስነልቦና ለተላበሰ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ግንባታ የመደመር መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ የተቋሙን የማድረግ አቅም በከፍተኛ ሁኔታ አሳድጓል። ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዓለም አቀፍ ደረጃ የውጊያ መልክ ተቀይሮ ወደ አራተኛው ትውልድ ጦርነት በመሸጋገር በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ በሰው አልባ አውሮፕላኖችና በሌሎች ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎች አቅምን ማጉልበት ቁልፍ ጉዳይ ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሀገር ብቻ ሳይሆን የምስራቅ አፍሪካ፣ የአፍሪካና የዓለም የሰላምና የጀግንነት ተምሳሌትነቱን በተግባር ያረጋገጠ ክንደ ብርቱ ኃይል ነው። በጥብቅ ወታደራዊ ዲሲፕሊን የሚመራው ይህ ጀግና ሰራዊት የኢትዮጵያን ጥቅምና ሉዓላዊነት ለመፈታተን ለሚዳዳቸው ማናቸውም የውስጥ ተላላኪዎችና የውጭ ላኪዎች ፈጣንና የማያዳግም ምላሽ በመስጠት ሰላምን በብርቱ ክንዱ የማረጋገጥ አቅሙ አለው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ሰራዊቱ የኢትዮጵያ ወኔና የጀግንነት ምልክት መሆኑን የገለጹት የሰራዊቱ ሁለንተናዊ የማድረግ አቅም መጎልበትም ኢትዮጵያ ሉዓላዊ አንድነቷን አስከብራ የምትቀጥል የክንደ ብርቱዎች ምድር መሆኗን ያመላክታል።

ይህ ጀግና የሀገር መከታ ሰራዊት ከጊዜ ወደ ጊዜ ሁለንተናዊ ዝግጁነቱን እያጠናከረ ይገኛል። ህዝባዊ ወገንተኝነቱንም በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ግዳጆች በተግባር አረጋግጧል፤ እያረጋገጠም ይገኛል። የኮሪያ፣ ኮንጎ፣ ሩዋንዳ፣ ኮትዲቯር፣ ቡሩንዲ፣ ላይቤሪያ እንዲሁም የሱዳን ዳርፉር ጋራና ተራራ፣ ሸለቆና ረባዳማ ስፍራ፣ ሜዳና ሸንተረር የጀግናው ሰራዊት ታሪክ ዘካሪ ሕያው ምስክሮች ናቸው። በአሁኑ ወቅትም በሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳንና ሱዳን ከቅድመ አያቶቹ የተረከበውን ለዓለም ሕዝብ ሰላምን የመቆም ታሪካዊ ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ ይገኛል።

ኢትዮጵያን ከከፍታ ማማዋ ለማሳነስ የግብፅ፣ ሻዕቢያና ሌሎች ታሪካዊ ጠላቶችን ተልዕኮ ያነገቡ የውስጥ ባንዳዎች ከንቱ ቅዠት በማምከን የሀገር አለኝታነቱን በተግባር የሚያስመሰክር ሰራዊት ነው። ኢትዮጵያ ሉዓላዊ አንድነቷንና ሰላሟን አስጠብቃ ለመቀጠሏ ምስጢሩ ይህ የሀገር ኩራት እና የትውልድ ባለአዳራ ሰራዊት መሆኑም በትውልድ ቅብብሎሽ ተገነባው አኩሪ የታሪክ ገድሉ ሕያው ምስክር ነው።

የአንዲት ሀገር ሁለንተናዊ የማድረግ አቅም ከሚለካባቸው መስፈርቶች መካከል አንዱ በመከላከያ ሰራዊት ግንባታዋ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይስማሙበታል። ለዚህም ነው የመከላከያ አጠቃላይ አቅሞች ኢትዮጵያ እያንሰራራች እና አስተማማኝ አቅም ላይ እንዳለች በግልጽ ያመላክታሉ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መግለጻቸው።

ለጎረቤት ሀገራት ሰላም እና ደህንነት መረጋገጥ የህይወት መስዋዕትነት ጭምር በመክፈል ወገንተኝነቱንና ጀግንነቱን በተግባር ማስመስከሩ ዓለም የሚያውቀው ተምሳሌታዊ ክንደ ብርቱ ሰራዊት ነው። በሁለንተናዊ የማድረግ አቅሙ የሚታወቀው ይህ የሀገር መከታ ትላንት ላይ ተቸክለው ለቆሙ ማናቸውም ኋላ ቀር ስብስቦች ፍቱን መድኃኒት ነው። ከታሪካዊ ስህተቱና ከሀገር ከሃዲነቱ ያልተማረው ሕገወጡ የሕወሓት ጠባብ ቡድን ከዚህ ጀግና ሰራዊት ፊት መቆም ከቶውንም አይችልም። ይህም በተደጋጋሚ ታይቷል።

የዚህ ጠባብና ተላላኪ ቡድን እኩይ ተግባር “ካልጠገቡ አይዘሉ ካልዘለሉ አይሰበሩ” ዓይነት ሆነና በሀገር መከላከያ ሰራዊት በተወሰደበት ፈጣን እርምጃ ድራሹ ጠፍቷል። የአኩሪ ገድል ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ዛሬም እንደ ትላንቱ በስልጣንና በዘረፋ ስካር ውስጥ ለተዘፈቀውና ሀገር ለማፍረስ ከውስጥ ባንዳዎችና ከውጭ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመሆን ለተከተለው የጥፋት መንገድ ሁሉንም በሚያስተምር መልኩ ፈጣን ምላሽ የመስጠት ሀገር የማጽናት ተልዕኮውን በብቃት የመወጣት ተግባሩን በጀግንነት ቀጥሏል።

ዛሬም ሆነ ወደፊት የኢትዮጵያ ብቸኛ መሻት ልማትን ማፋጠንና የቀጣናውን ሀገራት በኢኮኖሚ በማስተሳሰር የጋራ ብልፅግናን ማረጋገጥ ነው። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት ላይ ለሚቃጡ ማናቸውም የውስጥና የውጭ ትንኮሳዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚችል የሰላምና ደኅንነት ተቋም መገንባቱም መከላከያ ሰራዊት ሁነኛ አብነት ነው።

በዚህ መሠረት ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የወታደራዊ ተቋሟን የማድረግ አቅም በላቀ ደረጃ እያሳደገች ትገኛለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አሁን ላይ ኢትዮጵያ የታጠቀቻቸው በሰው ሰራሽ አስተውሎት እና በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች የታገዙት ድሮኖች ጦርነትን ማስቀረት ብቻ ሳይሆን ጦርነትን ባጠረ ጊዜ መጨረስ የሚያስችሉ ናቸው ሲሉ መግለጻቸው።

የኢትዮጵያ የታሪክ ድርሳናት ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟንና ሉዓላዊነቷን ለመግፈፍ የሚመጡ የውጭ ወራሪዎችንና የሚሰነዘሩ ማናቸውም ጥቃቶችን በድል አድራጊነትና ሉዓላዊነቷን ከማስከበር የማትበገር ሀገር መሆኗን ያመላክታሉ። ለዚህ ነው አባቶቻችን “ኢትዮጵያን የነካ የለውም በረካ” ሲሉ የሚገልጹት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተደጋጋሚ ኢትዮጵያ ትፈተናለች እንጂ አትሸነፍም ሲሉ መደመጣቸውም ይህንን መሠረት በማድረግ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም