የድል ከፍታን በሞራል ልዕልና ያጀበ ሕዝባዊ ሠራዊት - ኢዜአ አማርኛ
የድል ከፍታን በሞራል ልዕልና ያጀበ ሕዝባዊ ሠራዊት
ትልቅ ሀገር ፣ ትልቅ ህዝብ ፣ ታላቅ ርዕይ
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከሕዝብ አብራክ የወጣ፣ለሕዝብ ደኅንነትና ለሀገር ሉዓላዊነት የቆመ፣ሕዝብንም ደጀኑ ያደረገ ተቋም ነው።ሀገርንና ሕዝብን የሚያውኩ ባንዳዎችንና ባዳ ኃይላትን የሴራና የጥፋት መረብ እየበጣጠሰ የሕዝብ አለኝታነቱን እያስመሰከረ ነው።
ጠንካራ ሠራዊትነቱ በዘመናዊ ትጥቁና በውጊያ አቅሙ ብቻ ሳይሆን ከሕዝብ በተቀበለው አደራ፣ የሕዝብንና የሀገርን ደኅንነት በሚጠብቅበት ቁርጠኝነት፣ በሚያሳየው ሰብዓዊነትና በሚያስጠብቀው ሀገራዊ ክብር ጭምር የተረጋገጠ ነው።
ይህ የሠራዊቱ የሕዝባዊነት መርህ በዘመናዊ አደረጃጀቱ ውስጥ ባለፈባቸው ከምዕተ ዓመት የተሻገሩ ዓመታት ሀገሬውና ዓለም የመሰከረለት ነው። ከሀገር መከላከልና ሉዓላዊነትን ከማስጠበቅ ባሻገር፣ በተለያዩ ዘመናት ለሕዝብ ደኅንነትና ለሰብዓዊ አገልግሎት ባለው ቁርጠኝነትም ይወሳል። ይህ የልዕልና ታሪኩ በኢትዮጵያ ምድር ብቻ የተገደበ አይደለም።
በሶማሊያ፣ በላይቤሪያ፣ በኮንጎ፣ በዳርፉር፣ በአቢዬና በሌሎችም የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የኢትዮጵያ ሠራዊት ያሳየው ተሳትፎና ዲሲፕሊን የተሞላበት አበርክቶ በአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ውስጥ ያለውን ሚና ያስመሰክራል።በእነዚህ ተልዕኮዎች ውስጥ ሠራዊቱ የተሸከመው አደራ የሀገሩን ስም ከማስጠራት ባሻገር ለሰላም የሚደረገውን የአፍሪካ የጋራና የወንድማማችነት ጥረትም ከፍ ያደረገ ሆኗል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሕዝባዊነቱን ዛሬም የሀገርን ዳር ድንበር በሚያስከብርባቸው ቦታዎች ሁሉ በተጨባጭ ሥራዎቹ እያሳየ ነው። ሠራዊቱ የድል ከፍታን በሞራል ልዕልና፣ ወታደራዊ ብቃትን በዲሲፕሊን፣ የጥንካሬ መገለጫንም በሰብዓዊነት በማጀብ እያሳየ ያለው ጥረት የሚደንቅ ነው።የአሸናፊነት ልዕልና በሌላው ላይ በሚኖር ወታደራዊ ብልጫ ብቻ አይገለጽም፤ ከአሸናፊነት ጋር የሚመጣውን ኃላፊነት በጥበብ፣ በሕግና በሰብዓዊነት በመወጣትም ጭምር ይመዘናል።
ሠራዊቱ ሕገወጥና ጽንፈኛ ቡድኖች የሚፈጽሙትን ትንኮሳ በማምከን ሰላምን እያጸና፣ የሕዝብን ደኅንነት እየጠበቀ፣ሕብረተሰቡ የተለመደ ማኅበራዊ ኑሮውን ያለምንም ስጋት እንዲመራ እያደረገ ያለው ሚና የሕዝባዊነቱ ጉልህ መገለጫ ነው።ሠራዊቱ ሕዝቡ ውስጥ ገብቶ፣ሕዝቡን አረጋግቶ፣ ከሕዝቡ ጋር በመሆን አካባቢውን ከጥፋት ኃይሎች ሲያጸዳ ያሳየው ሙያዊ ሥነ ምግባር የኢትዮጵያን ጠንካራ ተቋማዊ አቅም የሚያመላክት ነው።
የኢትዮጵያ የድል አብሳሪ የሆነው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የ130 ሚሊዮን ሕዝብ ሀገርን፣ ግዙፍ ኢኮኖሚ እየገነባች ያለች ሀገርን፣ የቀጣናው መልህቅና የአፍሪካ ተምሳሌት የሆነች ትልቅ ሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅም ዛሬ ራሱን በግዙፍ የሰው ኃይል፣ በሥልጠና ብቃትን፣ በፈጠራ ቴክኖሎጂን ታጥቆ የወትሮ ዝግጁነት ላይ ይገኛል።የታሪካዊ ጠላትን የጥፋት አጀንዳ የተሸከሙ ባንዳዎችን አከርካሪ በመስበር ሀገርን በክብር የልማት ሥራዋን እንድታፋጥን አይተኬ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
መከላከያ ሠራዊት አሁን የዕድሜውን ያህል ራሱን ከዘመኑ ጋር እያራመደ ይገኛል። በራስን መቻል የመደመር መንግሥት ስትራቴጂ መሠረት ከቀላል የጦር መሣሪያዎች ጀምሮ የተራቀቁ የድሮን ቴክኖሎጂዎች ማምረት ጀምሯል።ከሆሚቾ የተተኳሽ መሣሪያዎች እስከ ስካይዊን የድሮን ማምረቻ ድረስ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎችን በማንቀሳቀስና በማምረት ለሌሎች ሀገራትም የሚተርፍ አቅም እየገነባ ነው።
ጦርነትን ከሩቅ የሚያስቀርና ውጊያን በፍጥነት የሚጨርስ ግዙፍ ሠራዊት የገነባችው ኢትዮጵያ መዳከሟን የሚመኙ፣ አትችልም የሚሉትን ሁሉ በድሎቿ እየረታች ጉዞዋን ቀጥላለች።በአራቱም አድማስ ሰላማዊነትን በማስቀደም የሚተነኩሷትን ደጋግመው እንዲያስቡ በሚያደርግ ጠንካራ እርምጃዋ እያሳፈረች ትገኛለች። ሠራዊቱም የሀገርን ጥቅምና ደህንነት በሁሉም አውድ በአስተማማኝ እያስጠበቀ ነው።
የሀገር ብሔራዊ ጥቅም ከባሕር የሚመነጩ ስጋቶችን በመቀነስም የሚረጋገጥ በመሆኑ የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት የትውልዱ የአርበኝነት ጥያቄን መሠረት በማድረግ የመርከቦቿንና የቀጣናውን ደኅንነት የሚያስጠብቅ ግዙፍ የባሕር ኃይል ገንብቷል።የሀገር ጥቅምና ደኅንነት በየብስና በባሕር ብቻ ሳይሆን በአየርም ጭምር የሚረጋገጥ እንደመሆኑ ሰማዩ የእኛ ነው በሚል መርህ 4ኛ ትውልድ ቴክኖሎጂን በመታጠቅ ወደ አምስተኛ ትውልድ ቴክኖሎጂ እየገሰገሰ የሚገኘውን ግዙፍ አየር ኃይል ያደራጀው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያን ደኅንነትና የአየር ክልል በአስተማማኝ ሁኔታ እየጠበቀ ይገኛል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊቱ የትልቅ ሀገርና የትልቅ ሕዝብ ሠራዊት ነው።በታላቅ ርዕይም ከሀገር እስከ ዓለም አቀፍ ተልዕኮዎች ራሱን እያበቃና እያዘጋጀ ጉዞውን ቀጥሏል።ሠራዊቱ ከሕዝብ አብራክ የወጣ የሕዝብ ልጅ ነው፤ ለሕዝብ ደኅንነት የቆመ የሕዝብ ጋሻ ነው፤ በችግር ጊዜ የሕዝብ ደጀን ነው።
የእውነተኛ ጀግንነት ልዕልናም ድልን በሰብዓዊነት፣ኃይልን በዲሲፕሊን፣ አሸናፊነትን በሞራል ጥንካሬ ማጀብ ነው።ይህ የሕዝባዊነት መንፈስ በተሰማራባቸው ሥፍራዎች ሁሉ ይታያል። ከሀገር እስከ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ የኢትዮጵያ ሠራዊት ምስጉንና ጀግና መሆኑ ሁልጊዜም ሲወሳ ይኖራል።