ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የካዳስተር ስርዓትን በመዘርጋት ህገወጥ የመሬት ወረራን የመከላከል ስራ በትኩረት እየተከናወነ ነው

ዲላ ፤ ጥቅምት 4/2019 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የካዳስተር ስርዓትን በመዘርጋት ህገወጥ የመሬት ወረራን የመከላከል ስራ ቅንጅታዊ በሆነ መልኩ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ መሬት አስተዳደር ቢሮ ገለጸ።

በክልሉ መሬትን በህጋዊ መንገድ የመመዝገብ፣ በአግባቡ የማስተዳደር እና ህገወጥነትን የመከላከል ስራ ላይ ትኩረት ያደረገ የምክክር መድረክ በዲላ ከተማ ተካሄዷል።


 

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ዳንኤል ዳሌ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ በክልሉ ውስን የሆነውን የከተማ መሬት በአግባቡና በዘመናዊ መንገድ ለማስተዳደር በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

በክልሉ በሚገኙ ከተሞች ከ58 ሺህ በላይ ያልተመዘገቡ የግል ይዞታዎች ተለይተው ህጋዊ የማድረጉ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

ቢሮው እስካሁን በአግባቡ ያልተመዘገቡና ህጋዊ የመሬት ይዞታዎችን ቆጥሮ በመለየትና በዘመናዊ መንገድ ዝርዝር መረጃዎችን በማደራጀት የመለየት ተግባር መከናወኑን ተናግረዋል።

ህግን ባልተከተለ መንገድ የተያዙ መሬቶችን በመለየት ወደ መንግስት መሬት ባንክ እንዲገቡ የማድረግ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የቢሮው ምክትል ኃላፊ ገልፀዋል።

ይህም ህገወጥነትን በመከላከል ለመልካም አስተዳደር ችግሮች ምላሽ ከመስጠት ባለፈ የመሬት ካዳስተር ስርዓትን ለመዘርጋት እያስቻለ መሆኑን አስረድተዋል።

በተለይ የከተሞችን የመሬት ሀብት በአግባቡ ማስተዳደርና ማዘመን የከተሞችን እድገት እያፋጠነ መሆኑንም አክለዋል።


 

የዲላ ከተማ መሬት አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ አቶ ምህረቱ አበበ በበኩላቸው፤ በከተማው በተያዘው በጀት ዓመት 429 ያልተመዘገቡ የግል ይዞታዎችን በመለየት ህጋዊ የማድረጉ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

ይህም በከተማው የሚገኙ መሬቶችን ሙሉ በሙሉ ወደ ካዳስተር ስርዓት ለማስገባት የሚደረገውን ጥረት እያገዘ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም