ቀጥታ፡

የዓለም አቀፍ የብድር ሽግሽግ አሰራር ፈጣንና ግልጽ የጊዜ ሰሌዳ ሊኖረው ይገባል - ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 4/2019 (ኢዜአ)፦ የዓለም አቀፍ የብድር ሽግሽግ አሰራር ፈጣንና ግልጽ የጊዜ ሰሌዳ ሊኖረው እንደሚገባ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ።

የ2026 የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ በታይላንድ ባንኮክ እየተካሄደ ነው።

ከዓመታዊው ስብሰባ ጎን ለጎን የዓለም አቀፍ የሉዓላዊ ብድር ውይይት ተደርጓል።

በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን የብድር ሽግሽግ ተሞክሮዎችን እና ልምዶችን አቅርበዋል።

የብድር ማቃለያ ጥያቄ ለሚያቀርቡ አዳዲስ ሀገራት ሂደቱ የተሳለጠ እና ግልጽ የሆነ የጊዜ ሰሌዳን የተከተለ መሆን እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።

በተጨማሪም በአበዳሪዎች መካከል የተሻለ ቅንጅት እንዲኖር እና ለማማከር አገልግሎት የሚፈጸሙ ክፍያዎች ገና ከጅምሩ ገደብ ሊጣልባቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።


 

ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የሉዓላዊ ብድር ውይይት መድረክ ቅድሚያ እንዲሰጥ የምትፈልጋቸውን ጉዳዮችንም አስቀምጠዋል።

አይኤምኤፍ እና የዓለም ባንክ እርስ በእርስ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

የብድር ሽግሽግ ካመጠናቀቁ በኋላ የብድር ምዘናቸው በጊዜያዊነት ዝቅ ላለ ሀገራት የተቀመጡ ጠበቅ ያሉ የብድር ማግኛ መስፈርቶችን ማሻሻል እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

ሀገራዊ የልማት እቅዶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመደገፍ የሚሰጡ አዳዲስ የፋይናንስ አቅርቦቶችን በቅንጅት መምራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በሁለቱ ተቋማት ዓመታዊ ስብሰባ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።

ልዑኩ ከስብሰባው ጎን ለጎን የተለያዩ ውይይቶችን በማድረግ ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም