ቀጥታ፡

የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና መርሃ ግብር የዲጂታል ዕውቀትና ክህሎታችንን እያዳበረልን ነው 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 4/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና መርሃ ግብር ከመደበኛው ትምህርት በተጨማሪ የዲጂታል ዕውቀትና ክህሎታቸውን እያዳበረላቸው መሆኑን በአዲስ አበባ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ

የመደመር መንግሥት በብዝኃ ኢኮኖሚ መርህ ቀርጾ ከተገበራቸው የግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድንና ቱሪዝም ዘርፍ የኢኮኖሚ ዕድገት አዕማዶች መካከል የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ አንዱ ነው።

የመደመር መንግሥት የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂም በሁሉም ዘርፍ የዜጎችን የዲጂታል ፈጠራ፣ ዕውቀትና ክህሎት በማበልጸግ የተቋማትን አገልግሎት እያሳለጠ ይገኛል።

በአዲስ አበባ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችና ርዕሰ መምህራን ለኢዜአ እንዳሉት፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ በዘርፉ ተወዳዳሪ ዜጋን መገንባት የሚያስችል አቅም እየፈጠረ ነው።


 

የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ከመደበኛው የመማር ማስተማር የትምህርት መርሃ ግብር በተጨማሪ የፈጠራ ዕውቀትና ክህሎታቸውን የሚያሻሽል ምኅዳር እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።

በለም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ኤልያስ ለገሰ፤ የትምህርት ቤታቸውን የአይሲቲ ቤተ-ሙከራ በመጠቀም የዲጂታል ዕውቀትና ክህሎቱን እያሳደገ መሆኑን ገልጿል።

በዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ መሠረት ተግባራዊ በተደረገው የአምስት ሚሊዮን ኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና መሠረት የፋንዳሜንታል ፕሮግራሚንግ ስልጠና መውሰዱን አስታውቋል።

ስልጠናውን መውሰዱም የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎቱን በማስፋት በሌሎች የስልጠና መስኮችን ጭምር ለመከታተል እንዳነሳሳው ተናግሯል።

በትምህርት ቤቱ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሜሮን አጥናው በበኩሏ፤ የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ተማሪዎች የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎታቸውን ለማሳደግ መልካም ዕድል መፍጠሩን ገልጻለች።

በዚህም በአምስት ሚሊዮን የኢትዮ-ኮደርስ የስልጠና መስኮች መካከል የዳታ ሳይንስ ስልጠና በመውሰድ በቀጣይም ሌሎቹን ለመሰልጠን ዕድሉን እንደምትጠቀም ተናግራለች።


 

የኢትዮጵያ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ልማት ስልጠና ከመደበኛ ትምህርት በተጨማሪ የፈጠራ ክህሎታችንን እያሳደገው ነው ያለው ደግሞ በድልበር አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ተማሪ አማኑኤል አዳነ ነው።

በተለይም ተማሪዎች ባሉበት ቦታ ሁሉ የዲጂታል ክህሎታቸውን የሚያሻሽሉበት መንገድ መኖሩ ተጨማሪ ዕውቀት የሚያገኙበትን ዕድል እንደፈጠረላቸው አንስቷል።

በትምህርት ቤቱ የ12ኛ ክፍል ተማሪ በአምላክ ቸርነት በበኩሏ፤ ቴክኖሎጂን ከትምህርቷ ጋር በማዛመድ ዓለም አቀፍ የዲጂታል ተወዳዳሪነቷን ለማጎልበት እየተጠቀመችበት መሆኑን ገልጻለች።

የዲጂታል ትምህርት መሠረተ ልማቶችም የማጠናከሪያ ትምህርት አማራጮችን የሚያገኙበት ወሳኝ ዕድል እንደፈጠረላቸውም ተናግራለች።


 

የድልበር አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዋና ርዕሰ መምህር ደጀኔ ተስፋዬ፤ ዓለም አቀፍ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ፈጣን ዕድገትን መሠረት በማድረግ የአይሲቲ ቤተ-ሙከራ ተደራጅቶ እየተሰራበት ነው ብለዋል።

በዚህም ተማሪዎች የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎታቸውን ማጎልበት የሚችሉበት የመማር ማስተማር የትምህርትና ስልጠና እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

የለም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዋና ርዕሰ መምህር ሰለሞን ዲሮ በበኩላቸው፤ በዲጂታል ክህሎት የዳበረ ዜጋ ለማፍራት ተማሪዎች የኢትዮ-ኮደርስና የአይሲቲ ትምህርትና ስልጠና እንዲወስዱ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም