ቀጥታ፡

በጽናትና በሕብር የተገነባች የጀግኖች ሀገር-ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ በታሪክ ሂደት ያጋጠሟትን ፈተናዎች በሚገባ በድል እየተወጣች ለዛሬ በቅታለች። ፈተናዎች ባጋጠሙ ቁጥር የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት ከመንግስት ጎን ተሰልፎ ሀገር የማጽናት ሚናውን በላቀ ደረጃ እየተወጣ ቆይቷል።

ዛሬም የኢትዮጵያ ህዝብ ከአባቶቹ እና ከአያቶቹ የወረሰውን የጀግንነት ታሪክ ሀገር ለማጽናት እና ልማትን ለማፋጠን እየተጠቀመበት ነው። በተለይም የዛሬው ትውልድ ልክ እንደ አባቶቹ ሀገር በማጽናት ተግባር ላይ እየተሳተፈ ይገኛል። ለዚህ ነው ኢትዮጵያ በጽናትና በአንድነት የተገነባች የጀግኖች ምድር ልትባል የሚገባት።

ኢትዮጵያ በረጅም የታሪክ ጉዞዋ በርካታ ፈታኝ ሁነቶችን፣ የውጭ ወረራዎችንና የውስጥ ውስብስብ ችግሮችን አልፋ ለዛሬ የበቃች ታላቅ ሀገር ናት። በየዘመናቱ ያጋጠሟት ፈተናዎች ሁሉ ሀገሪቱን የሚያፈርሱ ሳይሆን፣ ይልቁንም የህዝቧን ጥንካሬ፣ ጽናትና ሀገራዊ ፍቅር ይበልጥ አጎልብተው የሚያወጡ ሆነው አልፈዋል። ጠላቶቿ እንደሚመኙላትን መንገድ ሳይሆን ወዳጆቿን የምታኮራ ሀገር ሆና ቀጥላለች።

የኢትዮጵያ ህዝብ በታሪኩ የሀገሩ ነጻነት በተደፈረ፣ ህልውናዋም በተፈተነ ቁጥር ልዩነቶቹን ወደ ጎን በመተው ሀገር የማጽናት ታሪካዊ ሚናውን በላቀ ደረጃ ተወጥቷል። ከአድዋ ድል እስከ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፍጻሜ ኢትዮጵያውያን ‘አይችሉትም’፣ ‘አያደርጉትም’ የተባለውን ሁሉ ፈጽመው አይበገሬነታቸውን አስመስክረዋል።

በቅርብ ጊዜም የሀገር ህልውና ማስጠበቅ ላይ የታየው የህዝቡ አንድነት፣ ለሀገር ህልውና የሚከፈለውን መስዋዕትነት እና የጽናት ጥግ ያሳያል። ዛሬም ቢሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ከአባቶቹና ከአያቶቹ የወረሰውን የጀግንነት፣ የአይበገሬነትና የሀገር ፍቅር እሴት በመጠቀም ሀገር የማጽናትና የልማት ስራዎችን የማፋጠን ተግባሩን አጠናክሮ ቀጥሏል።

ለዚህ እንደምሳሌ የሚጠቀሱት የመደመር መንግሥት የልማት ውጥኖች የህዝቡን ተስፋ እና አንድነት የበለጠ ያለመለሙ፤ለፍጻሜያቸውም ታላቅ ቁርጠኝነት እየታየ ነው። በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያን በምግብ ራስን ለማስቻል እና ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በመተካት ወደ ውጭ መላክ የሚያስችል ትልቅ ሀገራዊ እንቅስቃሴ አሳክታለች። የደን ሽፋን መጨመር፣ የአፈር መሸርሸርን መከላከል፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን መቀነስ እና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ያለመ ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃ ውጥን በተከታታይ እየተገበረች ነው። በዚህ ሂደት የህዝቡ ተሳትፎ እና ንቃት በተጨባጭ ታይቷል።

በተጨማሪም አዲስ አበባን ጨምሮ በዋና ዋና ክልል ከተሞች የተጀመረ፣ የከተሞችን ጽዳት፣ ውበት፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እንዲሁም የተፈጥሮና የታሪክ ሀብቶችን በማልማት ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ላይ ማዋልና የቱሪዝም ዘርፍን ማሳደግ እና የኢኮኖሚ ስርዓቱን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ማድረግ፣ የዲጂታል ክፍያዎችን ማስፋፋት፣ የቴሌኮም ዘርፍን ክፍት ማድረግ እና የመንግስት አገልግሎቶችን በኦንላይን በማቅረብ ሂደት የህዝቡ የለውጥ ፍላጎትና ድጋፍ በገሃድ የታየ ነው።

በተለይም የዛሬው ሀገር ተረካቢ ወጣት በውስጥ እና በውጪ ጠላቶች በሚጎነጎኑ ሴራዎች ሳይሸወድና ሳይታለል፣ አባቶቹ ያቆዩለትን ሀገራዊ ፍቅርና ጀግንነት መነሻ በማድረግ በልማት፣ በሰላምና ሀገር በማጽናት ተግባር ላይ በንቃት እየተሳተፈ ይገኛል። ይህ ወጣቱ ላይ የሚንጸባረቀው የሀገር ፍቅር ስሜት ኢትዮጵያ ያሰበቻቸውን ማሳካት እንድትችል ከማድረግ ባለፈ በቀጣናውም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽኖ ፈጣሪ እንድትሆን ማረጋገጫ ማህተም ነው።

በመሆኑም፣ አባቶቻችን በደማቸውና በአጥንታቸው ያቆዩአትን ኢትዮጵያ፣ የዛሬው ትውልድ ደግሞ በእውቀቱ፣ በጉልበቱና ሕብረ ብሔራዊ አንድነቱን በማጽናት ለነገዋ የበለጸገች ሀገር የጣለውን መሰረት አጠናክሮ ይገነባታል።

ኢትዮጵያን የመገንባት የቅብብሎሽ ስራ ዛሬም በአንጸባራቂ ድል እየታጀበ ቀጥሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም