ከተሞች ወቅታዊ ፍላጎቶችን ከማሟላት ባለፈ ዘመን ተሻጋሪ ውርስ መተው በሚያስችል መልኩ መገንባት አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
ከተሞች ወቅታዊ ፍላጎቶችን ከማሟላት ባለፈ ዘመን ተሻጋሪ ውርስ መተው በሚያስችል መልኩ መገንባት አለባቸው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 4/2019 (ኢዜአ)፦የከተሞች ልማት ወቅታዊ ፍላጎትን ማሟላት ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱ ትውልድ የሚሻገር ዘላቂ ውርስ መተው በሚያስችል መልኩ መገንባት እንዳለበት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባዋ ይህንን ያሉት በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ ከንቲባዊ አመራር ኢኒሼቲቭ (African Mayoral Leadership Initiative) አባል ሀገራት የከተማ ከንቲባዎች ፎረም ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በንግግራቸው፤ አዲስ አበባ የጋራ ታሪክን በማቀናጀትና የወደፊት ተስፋን በመገንባት ላይ እንደምትገኝ ጠቁመዋል።
የከተማዋ ገጽታ በቤቶች ልማት፣ በመንገዶች፣ በትራንስፖርት፣ በዲጂታልና በሕዝብ አገልግሎቶች እንዲሁም በማኅበራዊ ልማት ኢንቨስትመንቶች አማካኝነት በከፍተኛ ደረጃ እየተቀየረ መሆኑንም ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አርቆ አስተዋይ አመራር የሚመራው የመደመር መንግሥት፤ ጥንካሬን በማቀናጀትና የጋራ ትብብርን በማጠናከር የተሻለና የጎላ ውጤት ለማስመዝገብ ትልቅ መሠረት መጣሉን ተናግረዋል።
የወደፊት ዕጣ ፈንታ ከልጆች እንደሚጀምር በመገንዘብ፣ አዲስ አበባን ሕፃናትን ለማሳደግ ከሁሉ የተሻለች የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝም አመላክተዋል።
ውጤት ተኮር አሠራሮችን በማጠናከር ከፍተኛ ለውጦች መመዝገባቸውንና የከተማዋ የገቢ አቅም በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መምጣቱንም አብራርተዋል።
የአፍሪካ ከተሞች እርስ በርስ በመማማር፣ አዳዲስ አሠራሮችንና ሃሳቦችን ወደ አካባቢያዊ እውነታዎች በማላመድ የነዋሪዎችን ሕይወት ማሻሻል እንደሚችሉ የጠቆሙት ከንቲባዋ፤ ሁሉም ከተሞች በዓላማ፣ በራዕይ እና ዘመን ተሻጋሪ ውርስ መተው በሚያስችል መልኩ ሊገነቡ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።