ቀጥታ፡

በክልሉ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የማር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እያደረገ ነው

ሆሳዕና፤ ጥቅምት 4/2019 (ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እየተተገበረ ያለው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የማር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕርግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በክልሉ እየተተገበረ ያለው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የማር ምርትና ምርታማነት በማሳደግ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እያደረገ ነው።


 

ባለፉት ዓመታት የሌማት ትሩፋት ፕሮግራሙን ተከትሎ የንብ ሀብት ልማቱን ከአረንጓዴ አሻራና ከተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ጋር አቀናጅቶ በተሰራው ስራ በርካታ የንብ መንደሮችን መፈጠር ተችሏል ብለዋል፡፡

በዚህም ከብዝሀ ሕይወት ጥበቃ ስራው በተጨማሪ በርካታ ዜጎችን በንብ ማነብ ሥራ በማሰማራት በዘርፉ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መምጣቱን ጠቁመዋል።

ባለፉት ዓመታት በመርሃ ግብሩ በተሰራው ሥራም የክልሉ ዓመታዊ የማር ምርት መጠን ከ3 ሺህ ቶን  ወደ 8ሺህ ቶን ለማሳደግ መቻሉንም  ሀላፊው አስረድተዋል።


 

በክልሉ የማር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል ምቹ ከባቢያዊ ምህዳር መኖሩን የገለጹት አቶ ኡስማን፣ በማር ምርት በባለፉት ዓመታት የተገኙ ውጤቶችን ለማስቀጠል የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ስድስት የአርሶ አደር የማር ማቀነባበሪያ ኢንዱስቱሪዎችን ወደ ተግባር ማስገባት የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

በክልሉ ሀድያ ዞን ሌሞ ወረዳ የታችኛው አምቢቾ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አለሙ ዳምጠው፤ የንብ ማነብ ስራቸውን ከመደበኛ ግብርና ስራቸው ጎን ለጎን እያስኬዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዚህም በየዓመቱ እስከ 60 ኪሎ ግራም የማር ምርት ለገበያ በማቅረብ ተጨማሪ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በሌሞ ወረዳ አምቢቾ ጎዴ ቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር ግርማ አሾሮ በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ አሻራ ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች  በንብ ማነብ ዘርፍ  ለተሰማሩ አርሶ አደሮች ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።


 

በግብርና ባለሙያ የተደረገላቸው ድጋፍ የንብ ማነብ ሥራቸውን ከባህላዊ ቀፎ ወደ ዘመናዊ ለማሸጋገር እንዳገዛቸውም ጠቁመዋል።

ይህም በዓመት እስከ 50 ኪሎ ግራም ማር አምርተው ለገበያ በማቅረብ ተጨማሪ ገቢ በማግኘት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም