በከተማ አስተዳደሩ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ621 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የልማት ስራ ተከናውኗል - ኢዜአ አማርኛ
በከተማ አስተዳደሩ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ621 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የልማት ስራ ተከናውኗል
ደሴ ፤ ጥቅምት 4/2019 (ኢዜአ)፦በደሴ ከተማ አስተዳደር በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ621 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የልማት ስራ መከናወኑ ተገለጸ፡፡
በክረምቱ ወቅት በተካሄደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ621 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የልማት ሥራዎች መከናወናቸውንም የከተማ አስተዳደሩ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ አስታውቋል።
የከተማ አስተዳደሩ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማጠናቀቂያና የ2019 የበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መድረክ ዛሬ በደሴ ከተማ ተካሂዷል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በከተማ አስተዳደሩ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተመዘገበው አበረታች ውጤት በበጋውም ወራት ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደ ሀገር የመተጋገዝ፣ የመተባበርና የአብሮነት ባህልን በማስቀጠል የዜጎችን ሁለንተናዊ ችግር ከማቃለሉ ባለፈ የልማት ክፍተቶችን መሙላት እያስቻለ ነው ብለዋል።
በበጋው ወቅት ለማካሄድ የታሰበው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበረሰቡን በተሻለ መንገድ ተጠቃሚ የሚያደርግ እንዲሆንም የተለያዩ እቅዶች ተግባራዊ እንደሚደረጉ ነው ያመለከቱት።
የከተማ አስተዳደሩ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሪት ትግስት አበበ በበኩላቸው፤ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለማቃለል ተችሏል ነው ያሉት።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከ181 ሺህ በላይ ዜጎችን በማሳተፍ ከ130 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።
በክረምቱ ወቅት የ296 አቅመ ደካሞችን ቤት በማደስና በአዲስ በመገንባት፣ 3ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል፣ 2 ሺህ 800 ዩኒት ደም የመለገስና ሌሎች ተግባራትን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማከናወን መቻሉንም ተናግረዋል።
በተጨማሪም ከ2 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አቅመ ደካማ ወገኖች ነጻ ምርመራና ሕክምና እንዲያገኙ ከማድረግ ባሻገር፣ 10 ሺህ ሄክታር የሚሆን የአቅመ ደካሞችን መሬት በማረስ በዘር የመሸፈንና የመንከባከብ ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል።
የተካሄዱት የበጎ ፈቃድ ሥራዎች በገንዘብ ሲተመኑ ከ621 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያስወጡ መሆናቸውን ጠቁመው፤ የክረምቱን ተሞክሮ በመቀመር በበጋው ወራት የላቀ አፈጻጸም ለማስመዝገብ እንደሚሰራ አስረድተዋል።
ከበጎ ፈቃደኞች መካከል ወይዘሮ የሺ ገዛኸኝ በሰጡት አስተያየት፤ በክረምት የነበረውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በበጋውም ወቅት ለመቀጠል ተዘጋጅተናል ብለዋል።
በመድረኩ የከተማና የክፍለ ከተማ አመራሮች፣ በጎ ፈቃደኞችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።