ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ከ400 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት የሚያስችል ንቅናቄ ተጀመረ

ደብረ ማርቆስ፤ ጥቅምት 4/2019 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል ከ400 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት የሚያስችል ንቅናቄ ተጀመረ፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የ2019 የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረክ በደብረ ማርቆስ ከተማ አካሂዷል።


 

የቢሮ ኃላፊው ዶክተር መስፍን አበጀ በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤ የበጋ መስኖ ልማት የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባለፈ ለገበያ የሚተርፍ ምርት ለማምረት እያስቻለ ነው። 

በዚህም አርሶ አደሩ የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ውሃን በመጠቀም የመስኖ ልማትን በማሳደግ ከዝናብ ጥገኝነት የተላቀቀ የአመራረት ዘዴ እንዲከተል በማድረግ ተጠቃሚ አድርጎታል ነው ያሉት።

በተያዘው የበጋ ወቅትም በሦስት ዙር ከ734 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በነባርና በአዲስ መስኖ በማልማት ከ95 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን አስረድተዋል።

ከሚለማው መሬት ውስጥም ከ400 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው በበጋ ስንዴ የሚለማ ሲሆን፤ ከ16 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል።

የታቀደውን ለማሳካትም ማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘርና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ከማቅረብ ባለፈ የባለሙያ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ፈጥኖ ወደ ልማቱ እንዲገባ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።


 

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዋለ አባተ በበኩላቸው፤ የመስኖ ልማት ስራው የምግብ ዋስትናና የኢኮኖሚ ነፃነትን ለማረጋገጥ ሰፊ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ጠቁመዋል።

በተያዘው የበጋ ወቅትም ከ130 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ በማልማት ከ7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት እንዲቻል ወደ ሥራ መገባቱን አስረድተዋል።

የመስኖ ፕሮጀክቶችን በመጠገንና በማስተካከል ፈጥኖ ወደ ልማት ሥራው ለመግባት እየተሰራ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም