ቀጥታ፡

አዲስ አበባ ለአፍሪካ ከተሞች ተምሳሌት መሆን ጀምራለች- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 4/2019 (ኢዜአ)፦ አዲስ አበባ ለአፍሪካ ከተሞች ተምሳሌት መሆን ጀምራለች ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ በመልዕክታቸው፤ አዲስ አበባ ለሁለተኛ ጊዜ ያስተናገደችውን የአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎች አመራር ኢኒሼቲቭ (AMALI) የ2026 የአመራሮች ፎረም ተሳታፊዎችን ዛሬ መቀበላቸውን ጠቁመዋል።

ይህ መድረክ ልምድ ለመለዋወጥ፣ እርስ በርስ ለመማማርና ከተማችን እያካሄደች ያለውን የለውጥ ጉዞ ለማካፈል ጠቃሚ ዕድል መፍጠሩን አመልክተዋል።

የከተማችን የለውጥ ጉዞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አርቆ አሳቢነትና ለከተማዋ ባስቀመጡት ራዕይ የተቃኘ መሆኑን ገልጸው ይህንን ራዕይ ወደ ተጨባጭ የልማት ውጤቶች እየቀየርን ነው ብለዋል።


 

በትራንስፖርት፣ በቤቶች ልማት፣ በቴክኖሎጂ የተደገፉ አገልግሎቶችና በትውልድ ግንባታ ላይ በምናከናውናቸው ሥራዎች የነዋሪዎቻችንን ተጠቃሚነት እያረጋገጥን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በራሳችን የፋይናንስና የዕውቀት አቅም ላይ ተመሥርተን በመሥራታችን፣ የአዲስ አበባ ተሞክሮ ለሌሎች የአፍሪካና የዓለም ከተሞች ጠቃሚ ትምህርቶችን እያበረከተና አዳዲስ የልማት ዕድሎችን እያመላከተ መሆኑ አስደሳች መሆኑን ነው የገለጹት።

በተለይም አዲስ አበባን በአፍሪካ ህፃናትን ለማሳደግ ምርጥ ከተማ ለማድረግ ያለንን ጽኑ ቁርጠኝነት እያሳየን እንገኛለን ብለዋል።

በሕፃናት እድገት (ECD) ላይ ያተኮሩ ተግባራትን በማጠናከር፣ የሕፃናትን ደህንነት፣ ትምህርትና የወደፊት ሕይወት በከተማችን የልማት አጀንዳ ማዕከል ላይ አስቀምጠናል ሲሉ ተናግረዋል።

ከየአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎች አመራር ኢኒሼቲቭ (AMALI) መሪዎችና የፎረሙ ተሳታፊዎች ጋር በመሆን፣ በከተማችን በልዩ ሁኔታ የተገነባውንና ለፕሮግራሙ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ባደረገችው ሊዛ ዲዬጎ መታሰቢያ የተሰየመውን የሕፃናት እንክብካቤ ማዕከል ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን አመልክተዋል።

ከንቲባዋ ለዚህ መርሐ ግብር ስኬት አስተዋጽኦ ላደረጉት የቢግ ዊን ፊላንትሮፒ መሥራች፣ ሊቀመንበርና ፕሬዝዳንት ጄሚ ኩፐርን፣ የፋውንዴሽኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱ፣ አማካሪዎችና የፕሮግራሙን አመራሮች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም