ቀጥታ፡

በሸገር ከተማ የመሶብ አንድ ማዕከል ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት በመስጠት የተገልጋዩን እርካታ እያሳደገ ነው

ሸገር፣ ጥቅምት 04/2019 (ኢዜአ)፡- የሸገር መሶብ የአንድ ማዕከል ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት የህብረተሰቡን ፍላጎት በብቃት እያሟላ እንደሚገኝ የከተማ አስተዳደሩ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ገለጸ።

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተለያዩ ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎቶች በአንድ ጣራ ስር በማሰባሰብ ዜጎች ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ቆጥበው ለእንግልት ሳይዳረጉ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል የተጀመረ አሰራር ነው።

 
በኦሮሚያ ክልል በሸገር ከተማ አስተዳደርም የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስና አገልግሎትን ወደ ማህበረሰቡ ይበልጥ ለማቅረብ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በማስፋፋት ላይ ይገኛል።

አገልግሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ግልጽ፣ ተጠያቂነት ያለው እና ዘመናዊ ለማድረግ ፋይሎችን በዲጂታል በተደራጀ መልኩ በመያዝ በአጭር ደቂቃዎች ውስጥ አገልግሎት እየተሰጠ ያለ አሰራር ነው።

የከተማው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሳሁን ጆብር ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ በ2019 በጀት ዓመት በከተማው የማህበረሰቡን ፍላጎት ለማሟላት ዋናውን ማዕከል ጨምሮ አራት ቅርንጫፎች በመክፈት በአጠቃላይ በአምስት ማዕከላት በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋ አገልግሎት እየተሰጠ ነው።

በእነዚህ ማዕከላት በተደረገ እንቅስቃሴ፣ በአንደኛው ሩብ ዓመት አገልግሎት ለማግኘት ከቀረቡት 165 ሺህ 91 ዜጎች መካከል አስፈላጊውን መስፈርት ያሟሉ ከ161 ሺህ በላይ የሚሆኑት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በመሶብ የአንድ ማዕከል የአገልግሎት አሰጣጥ የማህበረሰቡን ፍላጎት 99 ነጥብ 9 በመቶ ማድረስ መቻሉን ጠቁመው፣ ይህም የህብረተሰቡን እርካታና ተጠቃሚነት በብቃት ማሳደጉን አረጋግጠዋል።

የተገልጋዮች ፋይል በተደራጀ መልኩ መያዙ አገልግሎቱን ቀልጣፋ አድርጎታል ያሉት ስራ አስኪያጁ፤ ይህም ህብረተሰቡ ለእንግልትና ለአላስፈላጊ ወጪ ሳይዳረግ ጊዜውን በአግባቡ በመጠቀም ሙሉ ትኩረቱን ወደ ልማት ስራዎች እንዲያዞር አስችሎታል ብለዋል።

በማዕከሉ በአማካኝ በ24 ደቂቃዎች ውስጥ ተገልጋዩ የሚፈልገውን አገልግሎት ማግኘት መቻሉን ያነሱት አቶ ካሳሁን፤ ይህ አሰራር የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታትና የልማት ሥራዎችን በማፋጠን የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው አብራርተዋል።

እንዲሁም ተበትነው የነበሩትን አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወደ አንድ ማዕከል በማምጣት በአጭር ጊዜ ውስጥ ግልጽና የተሟላ አገልግሎት በመስጠት፤ ማህበረሰቡ በመንግስት ላይ ያለውን እምነትና ተሳትፎ በተጨባጭ ማሳደጉን ጠቁመዋል።
 
በዚህም የመንግሥት ገቢን በማሳደግ፣ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ በማድረግ እና የተያዙ የልማት ግቦችን በማፋጠን ረገድ ማዕከሉ የጎላ ሚና ያለው መሆኑን አስገንዝበዋል።
 
በሸገር ከተማ የአገልግሎቱን ተደራሽነት ለማስፋት በሁሉም ክፍለ ከተሞች ማዕከላት እንደሚቋቋሙ የገለጹት አቶ ካሳሁን፣ በተያዘው በጀት ዓመትም ተጨማሪ አራት ማዕከላት ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም