በመደመር መንግስት የተፎካካሪ ፓርቲዎችን በማሳተፍ በጋራ ሀገርን የመገንባት ቁርጠኛ ነን- የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
በመደመር መንግስት የተፎካካሪ ፓርቲዎችን በማሳተፍ በጋራ ሀገርን የመገንባት ቁርጠኛ ነን- የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት
ሆሳዕና፤ ጥቅምት 4/2019(ኢዜአ)፦ በመደመር መንግሥት የተፎካካሪ ፓርቲዎችን በማሳተፍ በጋራ ሀገርን የመገንባት ቁርጠኝነት መኖሩን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለፀ።
የጋራ ምክር ቤቱ በመደመር መንግስት ምስረታና ቀጣይ በትብብር በሚሰሩ ተግባራት ዙሪያ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።
የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ደምስ ገብሬ በሰጡት መግለጫ፤ በመደመር መንግስት የተፎካካሪ ፓርቲዎችን በማሳተፍ በጋራ ሀገርን የመገንባት ቁርጠኝነት መኖሩን ገልጸዋል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ የመንግስት ምስረታውን ካከናወነው ብልጽግና ፓርቲ ጋር እንደከዚህ ቀደሙ በጋራ እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡
የመደመር መንግስት በሀገር ሰላምና ልማት መጠናከር ዙሪያ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመስራት የበለፀገች ሀገርን በጋራ ለመገንባት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ምስረታ ስለማከናወኑም ገልጸዋል፡፡
የጋራ ምክር ቤቱ በመደመር መንግስት የሚተገበሩ የህዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ የሰላም ማስጠበቅና የልማት ስራዎችን በትብብር በመስራት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንደሚወጣም ሰብሳቢው ገልጸዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ በረከት ከድር በበኩላቸው፤ የመደመር መንግስት በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ አካታችነትን ማዕከል ያደረገ መንግስት መመስረቱን ተናግረዋል።
ይህም በኢትዮጵያ የሀሳብ ብዝሃነትን መሰረት ያደረገ የትብብር ዴሞክራሲ ስርዓትን በመተግበር ረገድ ተምሳሌት እንደሚያደርገው ጠቅሰዋል።
በዚሀም በክልሉ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን ያሳተፈ የአመራር አደረጃጀት ከመፍጠር ባሻገር በምክር ቤቱ 27 መቀመጫዎች ለተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች ስለመለቀቃቸውም አስረድተዋል።
የመደመር መንግስት የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን በማካተት ከተናጠል ይልቅ በጋራ ሀገር ለመገንባት ያለውን ተነሳሽነት በምስረታው ማረጋገጡን የገለጹት ደግሞ የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ሊቀ መንበርና የምክር ቤቱ ፀሐፊ አቶ ፈድሉ ጁሃር ናቸው፡፡
ፓርቲያቸው አዲስ ከተመሰረተው መንግስት ጋር በቅንጅት በመስራት የሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደቱን የተሻለ ለማድረግ እንደሚሰራም ገልጸዋል።
በእናት ፓርቲ የሆሳዕናና አካባቢ ፀሐፊና የጋራ ምክር ቤቱ ስራ አስፈፃሚ አቶ ተመስገን ሹመቱ በበኩላቸው፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አሸናፊ የሆነው የመደመር መንግስት ምስረታ የዲሞክራሲ ባህልንና የመድብለ ፓርቲ መርህን ተከትሎ የተፈፀመ ነው ብለዋል፡፡