ቀጥታ፡

የምርምር ማዕከላት ምርታማነትን ለማሳደግና የህብረተሰቡን ህይወት ለመለወጥ ይበልጥ መትጋት ይገባቸዋል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 4/2017 (ኢዜአ)፦ የግብርና ምርምር ማዕከላት ምርታማነትን ለማሳደግና የህብረተሰቡን ህይወት ለመለወጥ ይበልጥ መትጋት እንደሚገባቸው የግብርና ሚኒስቴር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የምርምር አቅምን ለማጠናከርና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚረዱ ትራክተሮችና ኮምባይን ሃርቨስተሮችን ለክልል የምርምር ተቋማት አስረክቧል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስቴር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር)፤ የሀገሪቱን ግብርና ለማዘመንና ለማሸጋገር የምርምር ዘርፉ ወሳኝ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።

በምርምር የተገኙ ውጤቶችና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ይበልጥ ወደ አርሶና አርብቶ አደሩ ተደራሽ ከማድረግ አኳያ የተቀናጁ አሠራሮችን መተግበር እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

የግብርና ምርምር ማዕከላት ምርታማነትን ለማሳደግና የህብረተሰቡን ህይወት ለመለወጥ በጋራ እንዲሰሩም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ንጉሴ ደቻሳ (ፕ/ር) በበኩላቸው፤ ግብርና የህዝቡ የኑሮ ምንጭ፣ የምግብ ዋስትና እና የኢኮኖሚው መሰረት ነው ብለዋል፡፡

የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ ለአርሶ አደሩ ገቢ ማደግ፣ ለምግብ ዋስትና እና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።

ይህን ለማሳካትም የተሻሻሉ ዘሮችን፣ ግብዓቶችን፣ የመስኖ ልማትን፣ የቴክኖሎጂና የማሽነሪ አቅርቦትን ማመቻቸት አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል።

የግብርና ሜካናይዜሽን የሰው ጉልበትና ጊዜን ለመቆጠብ፣ ወጪን ለመቀነስና ምርታማነትን ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑንም አስረድተዋል።

የተረከቧቸው የግብርና ማሽነሪዎች የክልል ምርምር ተቋማትን አቅም በማጎልበት የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱም አብራርተዋል።

የግብርና ሜካናይዜሽን የሰው ጉልበትና ጊዜን ለመቆጠብ፣ ወጪን ለመቀነስና ምርታማነትን ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።

የተከፋፈሉት የግብርና ማሽነሪዎች የክልል ምርምር ተቋማትን አቅም በማጎልበት የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ አብራርተዋል።


 

የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አስማረ ደጀን (ዶ/ር) በሰጡት አስተያየት፤ ኢንስቲትዩቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ምርታማነትን የሚያሳድጉ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል።

የተደረገላቸው የትራክተርና የኮምባይነር ድጋፍ ጥራትን ለማሻሻልና እንግልትን ለማስቀረት ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ጠቁመዋል።


 

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ ተረፈ በበኩላቸው፤ የተደረገላቸው የትራክተር ድጋፍ ሰፋፊ ማሳዎችን በጊዜ ለማዘጋጀትና የትራክተር አቅምን ለማሳደግ እንደሚረዳ ተናግረዋል።

በዘመናዊ ማሽን የሚታረስ መሬት ከባህላዊው አሰራር በተሻለ በምርታማነትና በጥራት የላቀ በመሆኑ አርሶ አደሩን ከቴክኖሎጂ ጋር ለማስተዋወቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም