በአርብቶ አደሩ አካባቢ የተጀመረው የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም የተማሪዎችን የትምህርት ተሳትፎና ውጤታማነት አሳድጎታል - ኢዜአ አማርኛ
በአርብቶ አደሩ አካባቢ የተጀመረው የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም የተማሪዎችን የትምህርት ተሳትፎና ውጤታማነት አሳድጎታል
ጂንካ፤ ጥቅምት 4/2019 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኦሞ ዞን በአርብቶ አደሩ አካባቢ የተጀመረው የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም የተማሪዎችን የትምህርት ተሳትፎና ውጤታማነት ከማሳደግ አንጻር ሚናው የላቀ መሆኑ ተገለጸ።
የደቡብ ኦሞ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መልካሙ ሺበሺ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ በ188 ትምህርት ቤቶች ውስጥ የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም እየተካሄደ ነው።
በዚህም እስካሁን ድረስ 66 ሺህ 337 ተማሪዎች የምገባ ፕሮግራሙ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ይህም የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥና መቅረትን በማስቀረት በትምርት ጥራት ላይ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አመልክተዋል።
ፕሮግራሙ የአርብቶ አደሩን የትምህርት ተሳትፎና ውጤታማነት ከማሳደግ አንፃር ሚናው የላቀ መሆኑም አቶ መልካሙ ገልጸዋል።
በዞኑ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ከተጀመረባቸው መካከል የቀይ አፈር አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህርት ይሳለሙሽ ሽቱ በበኩላቸው እንዳሉት፣ ካለፉት ዓመታት ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም በተማሪዎች የትምህርት ተሳትፎና በትምህርት ጥራት ላይ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ ነው።
የክልሉ መንግስት የተለያዩ አካላትን በማስተባበር ዘንድሮም የምገባ ፕሮግራሙን ማስቀጠሉን ገልጸው፣ ፕሮግራሙ ወደትምህርት ቤት የሚመጡ ተማሪዎችን ቁጥር በየጊዜው እንዲጨምር አድርጓል ብለዋል።
በተለይ እንደ ቀይ አፈር ከተማ ባሉ አርብቶ አደር አካባቢዎች የተማሪዎች ምገባ መጀመሩ ለመማር ማስተማር ሥራው ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጾ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በደቡብ ኦሞ ዞን የበና ፀማይ ወረዳ የቀይ አፈር አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በበኩላቸው የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ትምህርታቸውን በተረጋጋ ሁኔታ ለመከታተል እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
ተማሪዎች እንደገለጹት በትምህርት ቤቱ የተጀመረው የምገባ ፕሮግራም ትምህርታቸውን ሳይቸገሩ ለመከታተልና ሙሉ ጊዜቸውን ለትምህርታቸው እንዲሰጡ አስችላቸዋል።
ከተማሪዎቹ መካከል የ6ኛ ክፍል ተማሪ ሷሊ ሰኢድ፤ በትምህርት ቤቱ የተጀመረው የምገባ ፕሮግራም የተማሪዎችን የትምህርት ፍላጎት በማሳደግ ውጤታማ እንዲሆኑ እያደረገ ነው።
በተለይ ቁርስ ለመብላት በቤታቸው ያባኩኑት የነበረውን ጊዜ በማስቀረት በመግቢያ ሰዓት በትምህርት ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዲገኙ እንዳስቻላቸው ገልጻ፣ ይህም ትምህርታቸውን በተሻለ መልኩ ለመከታተል እንዳስቻላቸው ተናግራለች።
ሌላዋ የዚሁ ትምህርት ቤት የ6ኛ ክፍል ተማሪ አድናቆር አክሊሉ በበኩሏ ምግብ ሳይበላ የሚመጣ ተማሪ ትምህርቱን በአግባቡ ለመከታተል ይቸገራል ብላለች።
የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም መጀመሩ ይህን በማስቀረት ተማሪዎች ከትምህርት ቤት እንዳያረፍዱና እንዳይቀሩ ከማድረግ ባለፈ ትምህርታቸውን ተረጋግተው እንዲማሩ አስችሏል ብላለች።