ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ የፖሊሲ ማሻሻያ የዓለም አቀፍ ባንኮችን የኢንቨስትመንት ፍላጎት እያሳደገ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 4/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ የፖሊሲ ማሻሻያ የዓለም አቀፍ ባንኮችን የኢንቨስትመንት ፍላጎት እያሳደገ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሱፐርቪዥን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍሬዘር አያሌው ገለጹ።

✍️ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ

ዳይሬክተሩ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የባንኪንግ ኢንዱስትሪ ለኢኮኖሚ ልማት ውጤታማነት አስተዋጽኦ የሚያደርግበትን አካታችና የዳበረ የአሰራር ሥርዓት እንዲላበስ ተደርጓል።

በሀገር በቀል የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብርም ዓለም አቀፍ ባንኮችና የባንኪንግ ዘርፍ ተዋናዮች በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የሚሰማሩበት የፖሊሲ ውሳኔ መተላለፉን አስታውሰዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በባንኪንግ ዘርፍ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ አስቻይ የሕግና የፖሊሲ ከባቢ በመፍጠር እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ይህም የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን በመፍጠርና የዓለም አቀፍ ባንኮችን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የሚያበረታታ ምቹ ምኅዳር መፍጠሩን ተናግረዋል።

የዓለም አቀፍ ባንኮች ፈቃድ አሰጣጥና ስትራቴጂክ ኢንቨስተር ተቋማትን ተቀብሎ ወደ ኢንዱስትሪው ማሰማራት የሚያስችል የመግቢያ ማዕቀፍ መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል።

የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማነት በማስጠበቅ ውጤታማ ተወዳዳሪነትን የሚያስቀጥል አስፈላጊና ተገቢ የደኅንነት ማዕቀፍ መዘርጋቱንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ዓለም አቀፍ የባንክ ኢንቨስትመንትን ማስተናገድ የሚያስችል ብቁ የሰው ኃይል፣ የቴክኖሎጂ፣ የቁጥጥርና የክትትል ሥራን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በፋይናንስ ኢንዱስትሪ ዘርፉ የተፈጠረውን አስቻይ የኢንቨስትመንት ምኅዳር በመጠቀም በኢትዮጵያ ገበያ ለመሰማራት ፈቃድ መውሰድ የጀመሩ የውጭና የዓለም አቀፍ ባንኮች መኖራቸውን አስታውቀዋል።

ይህም የኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ የፖሊሲ ማሻሻያ ውጤታማነትን በማላቅ የዓለም አቀፍ ባንኮችን የኢንቨስትመንት ፍላጎት እያሳደገ መምጣቱን የሚያመላክት እንደሆነ ገልጸዋል።

በተጨማሪም የውጭ ባንኮች ከሀገር ውስጥ ባንኮች ጋር በሽርክና እና በአክሲዮን ኢንቨስትመንት ለመሥራት የስምምነት ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም በቅርቡ የተለያዩ የውጭና ዓለም አቀፍ ባንኮች በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ የኢንቨስትመንት አማራጮች የሚሰማሩበት ዕድል እንደሚፈጠር ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት የሚሰማሩ ባንኮችም የረጅም ጊዜ ዕቅድና ዓላማ ሰንቀው የሚሰማሩና ስትራቴጂክ ፋይዳ ያላቸው መሆናቸውን አንስተዋል።

ይህም የፋይናንስ ዘርፉን በቴክኖሎጂ፣ በአሰራርና በዕውቀት ሽግግር በማዘመን ጤናማ የውድድርና የአገልግሎት ውጤታማነትን ለማላቅ ጉልህ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም