ቀጥታ፡

አይኤምኤፍ ለኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ሽግግርና እድገት የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል አረጋገጠ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 4/2019 (ኢዜአ)፦ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ለኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ሽግግርና እድገት የሚያደርጋውን ድጋፍ በዘላቂነት እንደሚቀጥል አስታወቀ።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና ዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ በታይላንድ ባንኮክ መካሄዱን ቀጥሏል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በዓመታዊው ስብስባ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።

ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከዓመታዊው ስብስባው ጎን ለጎን ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናይጀል ክላርክ ጋር ውይይት አድርገዋል።

ናይጀል ክላርክ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳን ለማስቀጠል ያላት ጠንካራ ተነሳሽነት፣ ጥረት እና ጽናት አድንቀዋል።

ሀገሪቱ ያጋጠሟትን ፈተናዎች በሚገባ በመቋቋም ያሳየችውን ቁርጠኝነት እና የለውጡን አቅጣጫ ጠብቃ የመቀጠል አቅሟን አጽንኦት ሰጥተው አንስተዋል።

በተጨማሪም ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፣ አይኤምኤፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር እና ለሀገሪቱ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ሽግግርና እድገት የሚያደርገውን ዘላቂ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም