ባህር ዳር የጣና ፎረም እንግዶቿን ለመቀበል ተዘጋጅታለች - ኢዜአ አማርኛ
ባህር ዳር የጣና ፎረም እንግዶቿን ለመቀበል ተዘጋጅታለች
ከኢትዮጵያ የተፈጥሮ ውበት ማሳያዎች መካከል የምትጠቀሰው፣ የጣና ሐይቅ ፈርጥና የአባይ ወንዝ መሰረት የሆነችው ባህር ዳር ለ12ኛው የጣና ፎረም ታዳሚዎቿን በክብር ለመቀበል እጇን ዘርግታ እየጠበቀች ትገኛለች። በጣና ሐይቅ ውበት፣ በዛንባባዎቿ አጀብ፣ በኮሪደር ልማቷ ፈክታና ደምቃ እንግዶቿን አርሂቡ እያለች ትገኛለች።
የጣና ፎረም የተሰናዳባት ባህር ዳር ከተማ ከመስተንግዶም በላይ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት፣ የቱሪዝም አቅሟንና የሕዝቡን እንግዳ ተቀባይነት የምታሳይበት መልካም አጋጣሚ ነው ማለት ይቻላል። በዚሁ መሰረትም የጣናን ውበት በጣናነሽ እና ሌሎችም ዘመናዊ ጀልባዎቿ ለማስቃኘት፣ የቱሪዝም መስህቦቿን ለማስጎብኘት፣ በኢትዮጵያዊ መስተንግዶ አብልቶና አጠጥቶ አስደስቶ ለመሸኘት የተሟላ ዝግጅት ተደርጓል።
ከጥቅምት 13 እስከ 15 ቀን 2019 ዓ.ም. «በአፍሪካ የሰላም መንገዶች፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የጂኦፖለቲካ ለውጥ» በሚል መሪ ሐሳብ የሚካሄደው 12ኛው የጣና ፎረም ከ250 በላይ ተሳታፊዎች እንደሚገኙበት ይጠበቃል። በመድረኩም የአገራት መሪዎች፣ የተቋማት ኃላፊዎች፣ የቀድሞ መሪዎች፣ ምሁራንና ባለሙያዎች የሚመክሩ ይሆናል።
በመሆኑም በዚህ ታላቅ መድረክ ላይ የታደሙ እንግዶች የጣና ሐይቅን ልዩ ውበትና የቱሪዝም አቅም፣ የአካባቢውን የታሪክ፣ የባህልና መንፈሳዊ ቅርሶች መስህብ የመጎብኘት እድል ይኖራቸዋል። በተጨማሪም የከተማዋ ኮሪደር ልማት፣ የአረንጓዴ ስፍራዎችና የመዝናኛ ቦታዎች ቀልብን የሚገዙ ሆነው ያገኟቸዋል። በመሆኑም ባህር ዳር ከጣና ፎረም በተጓዳኝ የቱሪዝም አቅሟን የምታስተዋውቅበት እንደሚሆን ይጠበቃል።
የአንድ ከተማ ውበት በሕንፃዎቿ፣ በመንገዶቿና በተፈጥሮ ሀብቷ ብቻ አይመዘንም። ለእንግዶቿ በምታሳየው አክብሮት፣ በነዋሪዎቿ ደግነትና በሕዝቧ የባህል እሴቶችም ጭምር ይገለጻል። በዚህ ረገድ የባህር ዳርና አካባቢው ሕዝብ ያለው እንግዳ ተቀባይነት ለከተማዋ ሌላ ተጨማሪ አቅም ሆኖ እናገኘዋለን።
እንግዳን ተቀብሎ በፍቅርና በአክብሮት ማስተናገድ፣ መንከባከብና መንገድ ማመላከት የኢትዮጵያውያን የቆየና ይበልጥ እየዳበረ የመጣ ውብ ባህል ነው። በጣና ፎረምም ይህ እሴት በተግባር የሚገለጽበት በመሆኑ የባህር ዳርና አካባቢው ህዝብ ሽር ጉድ ብሎ እንግዶቹን እየተጠባበቀ ይገኛል።
የጉባኤው ውጤት በውይይት አዳራሹ ብቻ ሳይወሰን፣ በከተማዋ ልማት፣ በአካባቢው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና በቱሪዝም ዘርፍ አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል። በመሆኑም የከተማዋ አስተዳደሩ፣ የቱሪዝምና የንግድ ዘርፎች፣ የመስተንግዶ ተቋማትና ማኅበረሰቡ በቅንጅት መሥራት ወሳኝ ነው። የከተማዋ ውበትና የሕዝቧ እንግዳ ተቀባይነት ከፎረሙ ዓላማ ጋር ተደምሮ መልካም ስም የሚገነባበት ይሆናል።
በጣና ሐይቅ ዳርቻ በውበት የምትደምቀው፣ በልማት የምትለወጠውና በእንግዳ ተቀባይነቷ የምትታወቀው ባህር ዳር እንግዶቿን በክብር ለመቀበል ዝግጁ ነች። የጣና ፎረም ታዳሚዎችም ከጉባኤው ባሻገር የጣናን ውበት እያደነቁ እየተዝናኑ መልካም ትዝታ የሚያተርፉ ይሆናል።
የአማራ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አባይ መንግስቴ፤ በባህር ዳር የጣና ፎረም ታዳሚዎችን ተቀብሎ ለማስተናገድ የተሟላ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
በባህርዳር ከተማ የሚገኙ ሆቴሎችና ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ተቋማትም ለፎረሙ የሚመጡ እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጁ ስለመሆናቸው ተናግረዋል።