ኢትዮጵያ ከዩጋንዳ - ተጠባቂው የሴካፋ ማጣሪያ ጨዋታ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከዩጋንዳ - ተጠባቂው የሴካፋ ማጣሪያ ጨዋታ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 4 /2019 (ኢዜአ)፦ በ17ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ኢትዮጵያ ከዩጋንዳ ጋር ዛሬ ጨዋታዋን ታደርጋለች።
የሁለቱ ሀገራት የምድብ ሁለት መርሐ ግብር ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ በኪጋሊ ፔሌ ስታዲየም ይካሄዳል።
ኢትዮጵያ ከትናንት በስቲያ ከብሩንዲ ጋር ባደረገችው የምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታ 3 ለ 0 አሸንፋለች።
ዘሚካኤል ምንያህል፣ አክረም አብዱሰላም እና አብዲሳ ጉተማ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ዩጋንዳ በመጀመሪያ ጨዋታዋ ብሩንዲን 8 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፋለች።
በአሜሪካዊው አሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር የሚመራው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተጋጣሚውን ካሸነፈ ወደ ግማሽ ፍጻሜው በቀጥታ ያልፋል።
የአቻ ውጤት ብሔራዊ ቡድኑን በምርጥ ሁለተኝነት ወደ ግማሽ ፍጻሜ ማለፍ የሚችልበት እድል አለ።
በጋናዊው ላሪስ ኪንግስተን የሚሰለጥነው የዩጋንዳ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ማሸነፍ ወይም አቻ መውጣት በቀጥታ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ያሳልፈዋል።
ጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በምድብ አንድ አዘጋጇ ሩዋን ከሱዳን ጋር ምሽት አንድ ሰዓት ላይ ጨዋታን ታደርጋለች።
በሌላኛው መርሐ ግብር ሶማሊያ ከኬንያ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።
የማጣሪያ ውድድሩ እስከ ጥቅምት 10 ቀን 2019 ዓ.ም ይቆያል።
በውድድሩ ከአንድ እስከ ሶስት የሚወጡ ሀገራት ሴካፋ ዞንን ወክለው በአፍሪካ ዋንጫ ይሳተፋሉ።
17ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ እ.አ.አ በ2027 በሞሮኮ አስተናጋጅነት ይካሄዳል። በውድድሩ ላይ 16 ሀገራት ይሳተፋሉ።