ማንችስተር ሲቲ ከፒኤስጂ እና ሮማ ከሪያል ማድሪድ : የሻምፒዮንስ ሊጉ ተጠባቂ መርሐ ግብሮች - ኢዜአ አማርኛ
ማንችስተር ሲቲ ከፒኤስጂ እና ሮማ ከሪያል ማድሪድ : የሻምፒዮንስ ሊጉ ተጠባቂ መርሐ ግብሮች
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 4/2019 (ኢዜአ)፦ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሊግ ምዕራፍ ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ይካሄዳሉ።
ምሽት አራት ሰዓት ላይ ማንችስተር ሲቲ ከፒኤስጂ በኢትሃድ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ የእግር ኳስ አፍቃሪያንን ቀልብ ስቧል።
ማንችስተር ሲቲ በመጀመሪያ ጨዋታው ፖርቶን 2 ለ 0 ረትቷል።
የባለፉት ሁለት የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድሮች አሸናፊው የፈረንሳዩ ፒኤስጂ ስሎቫን ብራቲስላቫን 6 ለ 1 ረምርሟል።
ሁለቱ ክለቦች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሲገናኙ የአሁኑ ለስምንተኛ ጊዜ ነው።
ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው ሰባት ጨዋታዎች ሲቲ በአራቱ ድል ሲቀናው ፒኤስጂ ሁለት ጊዜ አሸንፏል። በቀሪው አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።
በሰባቱ ጨዋታዎች ላይ ማንችስተር ሲቲ 11 ግቦችን ሲያስቆጥር ፒኤስጂ 10 ጎሎችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ቡድኖቹ ለመጨረሻ ጊዜ እ.አ.አ በ2024/25 የውድድር ዓመት በተገናኙበት ጨዋታ ፒኤስጂ 4 ለ 2 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
ጨዋታው ጠንካራ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ሮማ እና ሪያል ማድሪድ ምሽት አራት ሰዓት ላይ በስታዲዮ ኦሊምፒኮ የሚያደርጉት ጨዋታም ትኩረትን ስቧል።
የጣልያኑ ክለብ በመጀመሪያ ጨዋታው ከፊነርባቼ ጋር አንድ አቻ ተለያይቷል።
የ15 ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ሪያል ማድሪድ በበኩሉ ኢንተር ሚላንን በሜዳው አስተናግዶ 2 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
ክለቦቹ በሻምፒዮንስ ሊጉ ከዚህ ቀደም ካደረጓቸው 12 ጨዋታዎች ማድሪድ ስምንቱን በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። ሮማ ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ በቀሪው ጨዋታ ነጥብ ተጋርተዋል።
ለመጨረሻ ጊዜ በተገናኙበት የእ.አ.አ 2018/19 የውድድር ዓመት የምድብ ጨዋታ ሪያል ማድሪድ 2 ለ 0 አሸንፏል።
በሌሎች መርሐ ግብሮች ላስክ ከሊቨርፑል እና ፌይኖርድ ከኮሞ በተመሳሳይ ምሽት 1 ሰዓት ከ45 ላይ ይጫወታሉ።
አስቶንቪላ ከፊነርባቼ፣ ቦዶ ግሊምት ከቦሩሲያ ዶርትሙንድ፣ ሪያል ቤቲስ ከፖርቶ፣ ስሎቫን ብራቲስላቫ ከስቱትጋርት እና ሻካታር ዶኔስክ ከኤኢኬ አቴንስ በተመሳሳይ ምሽት አራት ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።