ቀጥታ፡

የመደመር መንግሥት ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን የማጎልበት ማዕከላዊ እሳቤ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 4/2019 (ኢዜአ)፦ የመደመር መንግሥት ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን የማጎልበት ማዕከላዊ እሳቤ አካታች የፖለቲካ ምኅዳርን በማስፋት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስከበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ምሁራን ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ

7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም ባካሄደው 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የምክር ቤቱ መመስረቻ 1ኛ መደበኛ ጉባዔው ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር)ን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሰይሟል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክትም፤ የመደመር መንግሥት አካታችነትንና አሳታፊነትን በማጎልበት የኢትዮጵያን ብልፅግና የሚያረጋግጥ መሠረት መጣሉን ገልጸዋል።

ብልፅግና ፓርቲ ለዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበት ባለው ቁርጠኝነት የመደመር መንግሥት የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎን እያሳደገ መሆኑንና ይህም ለብሔራዊ ጥቅም መጠበቅ አይነተኛ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በፈተናዎች የታጀበ ቢሆንም ሕዝቡ ያሳየው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመው የምርጫ ሂደቱ የዴሞክራሲ ባሕል እያደገ ስለመምጣቱም አመላካች ነው ብለዋል።

በምርጫ ሂደት አሸናፊና ተሸናፊ ሊኖር ቢችልም ኢትዮጵያ አሸናፊ እንጂ ተሸናፊ ዜጋ እንደማይኖራትና በወንድማማችነት መንፈስ የሀገርን ዕድገት ለማስቀጠል እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

በቀጣይም የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት ለማስጠበቅ በሁሉም መስክ በትብብር እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን እንዳሉት፤ የመደመር መንግሥት አካታችና አሳታፊ የፖለቲካ ምኅዳር የኢኮኖሚ ዕድገትን በማፋጠን ብሔራዊ ጥቅሞችን ለማስጠበቅ ጉልህ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝምና አስተዳደር መምህርና ተመራማሪ ተስፋዬ ጂማ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የመደመር መንግሥት የዴሞክራሲ ምኅዳርን በማስፋት በትብብር ላይ የተመሠረተ አውድ ፈጥሯል።

ይህ የትብብርና አንድነት እሳቤም የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልፅግና ለማፋጠን የተወሰደ ቁርጠኛ አቋም እንደሆነ ገልጸዋል።

የመደመር መንግሥት ማዕከላዊ እሳቤም ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ነው ያሉት ምሁሩ፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በማሳተፍ የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ማስፋቱም ትብብርን ለማጎልበት ጉልህ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

የመደመር መንግሥት የባሕር በር ባለቤትነትን ለማረጋገጥ ያቀረበው ፍትሐዊና ምክንያታዊ ጥያቄም የሉዓላዊነትና ሕልውና ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል። 

የሥነ-አመራርና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ጌትዬ ትርፌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የመደመር መንግሥት አካታች የአመራር መዋቅር አዳዲስ አመራሮችን ለማፍራት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።

አዲሱ አካታችና አሳታፊ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች መዋቅርም የኢትዮጵያን ፈጣን የዕድገት መሻት ለማፋጠን የሚያስችል አቅም ለማጎልበትም ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመንግሥት ምስረታ ወቅት ያስተላለፏቸው የቀጣይ የልማት የትኩረት መስኮችም ኢትዮጵያ ማሳካት የምትሻቸውን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎቶች ማዕከል ያደረጉ መሆናቸውን አንስተዋል።

ይህም የሀገር ውስጥ ስብራቶችን በማከም ቀጣናዊ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል አቅም የሚገነባ መሆኑንም አብራርተዋል።

በቀጣይም ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን የበለጠ በማጎልበት የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታን በማፋጠን ለሕዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በትኩረት መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም