የመደመር እሳቤ፡ ለአፍሪካ የጋራ ብልፅግና አዲስ መንገድ - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር እሳቤ፡ ለአፍሪካ የጋራ ብልፅግና አዲስ መንገድ
ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የነጻነት፣ የሉዓላዊነት እና የጥቁር ህዝቦች ኩራት ተምሳሌት በመሆን በአፍሪካ አህጉር ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ አላት።
ቅኝ ያልተገዛችው፣ ሉዓላዊነቷን ያላስደፈረችው እና ክብሯን አስጠብቃ ለዘመናት የቆየችው ኢትዮጵያ፤ አፍሪካውያንን ከቅኝ ግዛት ለመላቀቅ ባደረጉት ትግል ውስጥ ፋና ወጊ እና የነጻነት ተምሳሌት በመሆን ታሪካዊ አሻራዋን አሳርፋለች። ይህ ታሪካዊ ሚናዋ ዛሬም ድረስ በአዲስ መልክ እየቀጠለ ይገኛል።
የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እና የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት ምስረታ ላይ ትልቅ አሻራ ያላት ኢትዮጵያ የህብረቱ ዋና መቀመጫ በመሆን የአህጉሪቷ የዲፕሎማሲ መናኸሪያ ናት።
ሀገሪቱ የአፍሪካውያን ነጻነት እና ራስን መቻል የሚያቀነቅነውን የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ ነፍስ እንዲዘራና ህያውነት እንዲላበስ በማድረግ የአህጉሪቱ ትልሞች እውን እንዲሆኑ የላቀ ሚና ተጫውታለች። በታሪክ የታየው ይህ የፓን አፍሪካኒዝም ስንቅ፣ ዛሬ ላይ በመደመር ፍልስፍና ታድሶ ድንበር ተሻጋሪ አህጉራዊ ኃይል እየሆነ መጥቷል።
የአዲሱ የመደመር መንግሥት ምስረታ የሀገሪቱን የውስጥ ፖለቲካዊ ምዕራፍ የሚያድስ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም የመደመር እሳቤ የኢትዮጵያን ወሰን አልፎ ለመላው አፍሪካውያን የሚጠቅም አህጉራዊ ፍልስፍና መሆኑን በተግባር ያሳየበት ክስተት ነው።
መደመር ሀገሪቷ ያሏት መልካም እሴቶች ላይ መጨመርን፣ ጉድለቶችን መሙላትን፣ ያለፈውን ስህተት አርሞ መልካሙን ማስቀጠልን እና በጋራ ማደግን የሚያስተምር ሀገር በቀል ፍልስፍና ቢሆንም፣ ዛሬ ላይ ግን ድንበር ተሻግሮ ለአህጉራዊው የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ፣ ለአፍሪካ ህብረት መጠናከር እና ለአፍሪካውያን በራስ የመተማመን መንፈስ አዲስ መነቃቃትን እየፈጠረ ይገኛል።
ይህ እሳቤ ለአፍሪካ ጥንካሬ ያለው አንድምታ ከፍተኛ ነው። አፍሪካውያን ያላቸውን የተፈጥሮ እና የሰው ሀብት አስተባብረው በዚሁ ድንበር ተሻጋሪ የመደመር እሳቤ ከተመሩ፣ ከማንኛውም ጥገኝነት መውጣት ይችላሉ። ፍልስፍናው በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ግንኙነት በማጠናከር፣ ከፉክክር ፈንታ በትብብር ላይ የተመሰረተ አህጉራዊ ትስስርን ለመገንባት አስተማማኝ መሰረት እየሆነ ነው።
በዚህ ማዕቀፍ ስር ኢትዮጵያ «የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካውያን ይፈቱ» የሚለውን የጸና አቋሟን ይበልጥ አጠናክራለች። አዲሱ የመደመር መንግሥት አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው አቅምና እውቀት እንዲፈቱ የሚያስችሉ ስራዎችን በወሰን ተሻጋሪ ወንድማማችነት መንፈስ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል።
ይህ ድንበር የተሻገረው የመደመር እይታ አፍሪካውያን እንደ አፍሪካ ህብረት ያሉ አህጉራዊና ቀጣናዊ ተቋማት ላይ ያላቸውን እምነት የሚያጠናክር እና የውጭ ጣልቃ ገብነትን በጋራ ለመመከት የሚያስችል ትልቅ አህጉራዊ አቅም የሚፈጥር ነው።
በመሆኑም በመደመር ፍልስፍና የሚመራ ጠንካራ የኢትዮጵያ መንግስት ምስረታ ለአፍሪካ እድገት እና ሰላም የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ነው።
ጠንካራ ኢትዮጵያ ማለት ለአፍሪካ ቀንድ አስተማማኝ ሰላም፣ ለምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ትስስር ምሰሶ እና ለመላው አህጉሪቱ የነጻነት ፋኖስ ናት። የመደመር እሳቤ የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግሮ ለአህጉሪቱ መፍትሔ መሆን መቻሉ፤ አፍሪካውያን በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ እና በዓለም መድረክ ላይ የሚገባቸውን ክብርና ቦታ እንዲያገኙ ለማድረግ የጎላ ሚና ይጫወታል።