አምቦ ዩኒቨርሲቲ የተሻሻሉ የሰብልና የእንስሳት ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች በማቅረብ ተጠቃሚ እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አምቦ ዩኒቨርሲቲ የተሻሻሉ የሰብልና የእንስሳት ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች በማቅረብ ተጠቃሚ እያደረገ ነው
አምቦ፤ ጥቅምት 3/2019 (ኢዜአ)፡-አምቦ ዩኒቨርሲቲ የተሻሻሉ የሰብል እና የእንስሳት ዝርያዎችን ለአካባቢው ለአርሶ አደሮች በማስተዋወቅና በማቅረብ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያሳድጉ እያገዘ መሆኑን አስታወቀ።
በዩኒቨርሲቲው ጉደር ማሞ መዘመር ካምፓስ በምርምር እየተከናወኑ ያሉ የግብርና ሥራዎች በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የግብርና ባለሙያዎች እና ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች ዛሬ ተጎብኝቷል።
በዚህ ወቅት የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ብዙነሽ ሚደቅሳ እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲትው ከመማር ማስተማር ሥራው ጎን ለጎን የአካባቢውን ማህብረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ ሳይንሳዊ ምርምሮችን እያከናወነ ይገኛል።
በዚህም የተሻሻሉ የሰብል እና የእንስሳት ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች በማስተዋወቅና በማቅረብ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው በ2018/2019 የምርት ዘመንም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በ73 ሄክታር መሬት ላይ በምርምር የተሻሻሉ የጤፍ፣ ስንዴ፣ የበቆሎ፣ የባቄላ፤ እና የቦሎቄ ዘሮችን እያለማ መሆኑን ተናግረዋል።
ለአርሶ አደሩ የተሻሻለ ዝርያ ከማቅረብና ሙያዊ ድጋፍ ከመስጠት በተጨማሪ፣ በእፅዋት በሽታ ቁጥጥር ላይ ተግባር ተኮር ሥልጠና እየሰጠ መሆኑንም አንስተዋል።
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የጉደር ማሞ መዘመር ካምፓስ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር አማን ሪቂቱ በበኩላቸው፤ የመስክ ጉቡኝቱ ዋና ዓላማ የዩኒቨርሲቲው አዳዲስ የምርምር ውጤቶች እና የማሕበረሰብ አገልግሎቶችን ለማስተዋወቅና ተሞክሮ ለመለዋወጥ መሆኑን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው በምርምር የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ከመስጠት ባለፈ የሆሮ እና የቦራና የወተት ላሞችን ዝርያ በማዳቀል ለአካባቢው አርሶ አደሮች እያከፋፈለ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በግብርና ባለሙያዎች ሙያዊ ድጋፍ በመስጠት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የቶኬ ኩታዬ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ንጌሴ ለሊሣ በበኩላቸው ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ በድጋፍ ያገኙትን የቦሎቄ ምርጥ ዘር በግማሽ የእርሻ ማሳቸው ላይ እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡
ዩኒቨርሲቲው ምርጥ ዘር ከማቅረብ በተጨማሪ በመዳበሪያ አቅርቦት፣ በሰብል በሽታ ቁጥጥርና መሰል ሙያው እገዛዎችን በመስጠት ምርትና ምርታማነታችን እንዲጨምር እያገዘን ነው ብለዋል።
አርሶ አደር ተገኝ በፍቃዱ በዩኒቨርሲቲው ዝርያዋ የተሻሻለ የወተት ላም ድጋፍ እንደተደረገላቸው ገልፀው የወተት ምርታማነታቸውን ለማሳደግ ጠንክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።