ቀጥታ፡

ባለፉት ሶስት ወራት የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችን በማስፋፋት የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ተችሏል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3 /2019 (ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ሶስት ወራት የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችን በማስፋፋት የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ መቻሉን የከተማው ንግድ ቢሮ ገለጸ፡፡ 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የ2019 በጀት ዓመት  የሶስት  ወራት ዕቅድ አፈጻጸም እና ቀጣይ  ስራዎች በተመለከተ ከለተያዩ የባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ የመደመር መንግሥት ምስረታ ከተካሄደ በኋላ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ግምገማ ማከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ባለፉት ሦስት ወራት ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ፣ የሕዝቡን ቅሬታ የሚፈቱና በቂና ጥራት ያለው የምርት አቅርቦት የሚያረጋግጡ ፍትሃዊና ተወዳዳሪ አሰራሮች መከናወናቸውን አመልክተዋል። 

በሁሉም ዘመናዊና ሁለገብ የገበያ ማዕከላት እንዲሁም በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በርካታ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በስፋት እንዲቀርቡ መደረጉን ገልጸዋል።

የንግድ ሥርዓቱን የበለጠ ለማሳለጥና ሙሉ በሙሉ ወደ ኦንላይን ለማስገባት የተጀመሩ የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውንና የተሻሉ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቁመዋል።

በ2018 ዓ.ም የነበረውን የ98 በመቶ የነበረውን የንግዱ ማህበረሰብ አገልግሎት እርካታ የበለጠ ለማሻሻል ከታቀደው በላይ ለመፈጸም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

አዲሱ የመደመር መንግሥት ከተዋቀረ በኋላ በአዳዲስ አሠራሮች ትልልቅ ለውጦችን ለማምጣት እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ጥራት፣ ፍትሃዊነትና ተደራሽነትን መሠረት ያደረጉ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

የጉለሌ ክፍለ ከተማ ንግድ ጽሕፈት ቤት የሸማቾች መብት ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ፋሲል ዘውዱ፤ ባለፉት ወራት ጥራት ያላቸው የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለነዋሪዎች መቅረባቸውን ተናግረዋል።

እነዚህ የተከናወኑት ዘርፈ ብዙ ተግባራት ሸማቹንና ሻጩን ተጠቃሚ ያደረገ የተሻለ አፈጻጸም እንዲመዘገብ ማስቻላቸውን ጠቁመዋል።

የቄርቆስ ክፍለ ከተማ ንግድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ቅድስት ኃይሌ በበኩላቸው፤ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችን ተደራሽነት በማስፋት የከተማው ነዋሪዎች የተለያዩ ምርቶችን በየአካባቢው እንዲያገኙ መደረጉን ገልጸዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም