በሲዳማ ክልል አመራሩ ለህዝብ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ትኩረት መስጠት አለበት - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል አመራሩ ለህዝብ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ትኩረት መስጠት አለበት
ሀዋሳ፤ጥቅምት3/2019(ኢዜአ):-በሲዳማ ክልል ከመሰረተ ልማት መጓተትና ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት ጋር በተያያዘ የሚነሱ የህዝብ ጥያቄዎችን ለመፍታት አዲሱ የክልሉ አመራር ትኩረት መስጠት እንዳለበት ነዋሪዎች ገለጹ።
በክልሉ ለሚከናወኑ የልማትና መልካም አስተዳደር ተግባራት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
የመደመር መንግስት ምስረታና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ክልል አቀፍ የውይይት መድረክ ዛሬ በሃዋሳ ከተማ ተካሂዷል፡፡
በዚህ ወቅት ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደገለጹት፣ የመደመር መንግስት ምስረታን ተከትሎ በየደረጃው የሚደረጉ ህዝባዊ ውይይቶች የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለይቶ ወደተግባር ለመግባት ያስችላል።
አዲሱ የክልሉ አመራር በተለይ ከመሰረተ ልማት መጓተትና ፍትሀዊ የልማት ተጠቃሚነት ጋር በተያያዘ የሚነሱ የህዝብ ጥያቄዎችን ለመፍታት ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የሃገር ሽማግሌው አቶ ቶንጋላ ቶርጋ እንዳሉት የዛሬው መድረክ ከክልሉ አዳዲስ አመራሮች ጋር ለመተዋወቅና በልማት ሥራዎች ላይ የጋራ አቅጣጫ ለመያዝ ጠቀሜታ አለው።
አዲሱ የክልሉ አመራር የመንግስትና የህብረተሰቡን አቅም በማስተባባር ለህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት እንዳለበት ገልጸው፣ እንደነዋሪም ለክልሉ ልማትና እድገት መፋጠን የሚጠበቅብንን እንወጣለን ብለዋል።
በሃዋሳ ከተማ የሃዌላ ቱላ ክፍለ ከተማ ሴቶች ማህበር ሰብሳቢ ወይዘሮ ታየች አረጋ በበኩላቸው፤ የመንግስት ምስረታን ተከትሎ በየደረጃው እየተካሄዱ ያሉ ህዝባዊ መድረኮች በቀጣይ ስኬታማ የልማት ሥራ ለማከናውን የሚያስችሉ ናቸው።
ህዝቡ ከመሰረተ ልማት መጓተትና ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት ጋር በተያያዘ ጥያቄዎች እንዳሉት አስታውሰው፣ እነዚህ ጥያቄዎች እንዲፈቱ አዳዲሶቹ የክልሉ አመራሮች በቁርጠኝነት መስራት አለባቸው ብለዋል።
የመደመር መንግስት በሃሳብ የበላይነት የሚያምን በመሆኑ መሰል ህዝባዊ መድረኮች መቀጠል አለባቸው ያሉት ደግሞ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)ን ወክለው በመድረኩ የተሳተፋት አቶ አቻ ለገሰ ናቸው፡፡
ህዝባዊ ውይይቶች የፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋት ባለፈ የህዝብን ትክክለኛ የልማት ጥያቄዎች ለይቶ ምላሽ ለመስጠት አቅም መሆናቸውን ጠቁመው፣ ለህዝብ የልማት ተጠቃሚነት ከመንግስት ጋር በመቀራረብ እንደሚሰሩ አመልክተዋል።
የውይይት መድረኩን የመሩት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር መሳይ ኃይሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት ፤ በመደመር መንግስት ለህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ ይገኛል።
በክልሉ ከልማት፣ ከመልካም አስተዳደር፣ ከፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ ከስራ ዕድል ፈጠራና መሰል ጉዳዮች ጋር የተነሱ የህዝብ ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ታቅዶ ወደተግባር መገባቱንም ጠቁመዋል፡፡
ለዚህም በክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ጸጋ፣ የወጣቱን አቅምና የተለያዩ አካላትን ጭምር በማቀናጀት የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በውይይት መድረኩ የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ መምሩ ሞኬ፣ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሃገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል፡፡