ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ እሴት በመጨመር ወደ ኢንዱስትሪ ምርት ለመሸጋገር ለምታደርገው ሀገራዊ ጥረት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው - ኢዜአ አማርኛ
ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ እሴት በመጨመር ወደ ኢንዱስትሪ ምርት ለመሸጋገር ለምታደርገው ሀገራዊ ጥረት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3 /2019 (ኢዜአ)፦ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ ከጥሬ ማዕድን ሽያጭ በመውጣትና እሴት በመጨመር ወደ ኢንዱስትሪ ምርት ለመሸጋገር ለሚደረገው ሀገራዊ ጥረት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ብርሃኑ አለሙ (ዶ/ር) ገለጹ።
ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ
የመደመር መንግሥት የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ መዋቅር ከመሰረቱ ለማሻሻል በተገበረው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትኩረት ከሰጣቸው ዘርፎች መካከል ማዕድን አንዱ ነው።
የማዕድን ዘርፉን በቴክኖሎጂ ታግዞ በማልማት ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ያለውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ እና ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በሳም ፕሬሺየስ ሜታልስ መካከል በተደረገ አጋርነት በቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና የተገነባው ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ መስከረም 30 ቀን 2019 ዓ.ም ስራ መጀመሩ ይታወቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ይህ የማጣሪያ ፋብሪካ፤ በሀገር ውስጥ ምርት ላይ እሴት ለመጨመር፣ የኢትዮጵያን የማዕድን ዘርፍ ለማጠናከርና ኢትዮጵያን በውድ ማዕድናት ማጣሪያ ቀጣናዊ ማዕከል ለማድረግ ለተጀመረው ጉዞ ትልቅ ምዕራፍ ነው።
ይህ ውጥን ሀብቶቻችንን ከኢንዱስትሪ አቅም ጋር በማስተሳሰር ወጭ ንግድ ገቢን ለማሳደግ፣ የሰለጠነ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የጌጣጌጥ ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ፣ እንዲሁም ይበልጥ ግልጽ እና ተወዳዳሪ የሆነ የወርቅ እሴት ሰንሰለት ለመገንባት የመደመር መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
ከማዕድን ማውጣት እስከ ኢንዱስትሪ ሽግግር ድረስ የላቀ እሴት እየተፈጠረ መሆኑን ጠቁመው፤ ፋብሪካው በዓመት ከ600 ቶን በላይ ውድ ማዕድናትን የማንጠር አቅም እንዳለውም ተናግረዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ የወጪ ንግድ ገቢን በማሳደግ የንግድ ሚዛንን የሚያሻሽል መሆኑን ገልጸዋል።
የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ብርሃኑ አለሙ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ከመንግሥት የብዝሃ ኢኮኖሚ ዘርፎች መካከል የማዕድን ዘርፍ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።
የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያ በከበሩ ማዕድናት ያላትን እምቅ ሀብት ወደ ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በመቀየር ለሀገሪቱ ልማትና እድገት ለማዋል እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በሀገር በቀል ኢኮኖሚ እቅድ መሠረት የከበሩ ማዕድናትን ወደ ሥራ በማስገባት ረገድ ትልቅ አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቁመው፤ በቅርቡ የተመረቀው የቦሌ ለሚ ልዩ ኢኮኖሚ ቀጠና ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ መከፈት ለዚህ ትኩረት ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
ፋብሪካው መቋቋሙ ኢትዮጵያ ከጥሬ ዕቃ ሽያጭ ወጥታ ወደ አምራችነት ለመሸጋገር ለምታደርገው ጥረት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
የሀብት እሴት ሰንሰለትን በማሳደግ ወርቅን ከጥሬ ማዕድን ደረጃ በላይ በማቀናበርና በማጣራት የተሻለ የገበያ ዋጋ ያላቸውን ምርቶች ለማቅረብ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
የተጣራና የጥራት ደረጃው የተረጋገጠ ወርቅ ወደ ውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ገቢን ከፍ ለማድረግና የንግድ ሚዛንን ለማሻሻል ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል።
የማጣሪያ ፋብሪካው የሀገር ውስጥ የማዕድን አምራቾችን፣ አቅራቢዎችን እና የጌጣጌጥ አምራቾችን በማገናኘት የኢንዱስትሪ ልማትና የሥራ ዕድል ፈጠራን እንደሚያበረታታ ገልጸዋል።
ፋብሪካው ኢትዮጵያን በምሥራቅ አፍሪካ የውድ ማዕድናት ማጣሪያና ማቀናበሪያ ማዕከል በማድረግ ቀጣናዊ ተወዳዳሪነትን ለማጠናከርና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ በመንግሥትና በግል አጋርነት (PPP) መገንባቱ ስትራቴጂካዊ የሀብት አቅምና የቁጥጥር ማዕቀፍ ከግሉ ዘርፍ ቴክኖሎጂና ቅልጥፍና ጋር ለማቀናጀት ያስችላል ብለዋል።
ይህ የትብብር ሞዴል ትልቅ የኢንቨስትመንት ካፒታል የሚጠይቁ ፕሮጀክቶችን እውን በማድረግ የሀገሪቷን አጠቃላይ ልማትና እድገት በፍጥነት ለማፋጠን ትልቅ አርአያነት ያለው መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡