የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በኦሊምፒክ ማጣሪያ ወደ ቀጣዩ ዙር አለፈ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በኦሊምፒክ ማጣሪያ ወደ ቀጣዩ ዙር አለፈ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3 /2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ሁለተኛ ዙር የመልስ ጨዋታ ከሩዋንዳ ጋር አንድ አቻ ተለያይቷል።
በድሬዳዋ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ መሳይ ተመስገን በ31ኛው ደቂቃ ባስቆጠረችው ግብ ኢትዮጵያ መሪ ሆናለች።
ፍሎረንስ ኢማኒዛባዮ በ90ኛው ደቂቃ ለሩዋንዳ የአቻነቷን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፋለች።
ድሉን ተከትሎ ኢትዮጵያ በድምር ውጤት 2 ለ 1 በማሸነፍ ወደ ሶስተኛ ዙር አልፋለች።
ሉሲዎቹ በሶስተኛው ዙር ከታንዛንያ ጋር ይጫወታሉ።
ታንዛንያ ዳሬሰላም ላይ ዛሬ ባደረገችው የመልስ ጨዋታ ቦትስዋናን 6 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፋለች። በድምሩ የ7 ለ 0 ውጤት አስመዝግባለች።
የኢትዮጵያ እና ታንዛንያ የሶስተኛ ዙር መርሐ ግብር በየካቲት ወር 2019 ዓ.ም ይካሄዳል።
በአምስት ዙሮች በሚካሄደው ማጣሪያ ሁለት ሀገራት አፍሪካን ወክለው በኦሊምፒክ ውድድሩ ላይ ይሳተፋሉ።
በአጠቃላይ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች የሴቶች እግር ኳስ 12 ሀገራት የሚሳተፉ ይሆናል።