ቀጥታ፡

ምክክር የሀገር ሥር፤ ኢትዮጵያ የመግባባት ተራራን በምክክር የምታንጽ ሀገር!!

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ

ኢትዮጵያ የጥንታዊ ሥልጣኔ፣ የረጅም ዘመን ታሪክና በሕብር የተሸመነ የሕዝብ ብዝኅ ጸጋ የተቸራት ሀገር መሆኗ የአደባባይ ሐቅ ነው። የሕዝቦቿ ቱባ እሴቶች፣ መከባበር፣ አንድነትና አብሮነት ለዘመናት የዘለቁ ውድ ሀብቶቿ ናቸው። የገዳ ሥርዓትን ጨምሮ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ እንዲሁም ሌሎች የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቱባ የእርቅ ሥርዓቶችና የአብሮነት እሴቶች ሀገር በቀል የመግባባት ዴሞክራሲ ጸጋዎች ሆነው ዘልቀዋል።

እነዚህ  ሀብቶች የተቸራት ኢትዮጵያ በየዘመናቱ በነበሩ የተለያዩ መንግሥታት የፖለቲካ አስተዳደር ሥርዓቶች ምክንያት የተከሰቱ የአለመግባባት ስብራቶችን አስተናግዳለች። ይህም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና የመግባባት ዴሞክራሲ ላይ እንቅፋት በመፍጠር በዜጎች መካከል መጠራጠር እንዲነግስ አድርጎ ቆይቷል። በዜጎች መካከል በጊዜ ሂደት እየተንሰራፋ የመጣው አለመግባባትም የሀገርን እድገት በማቀጨጭ ለብሔራዊ ጥቅም ተጋላጭነት አሉታዊ ጫና አሳድሯል።

በዚህም በ2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ ማግስት የመደመር መንግሥት መሰረታዊ ሀገራዊ ስብራቶችን ለመጠገን መንገድ ከፍቷል። ለአብነትም የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት፣ በውጭ ሀገር የነበሩ ተቃዋሚ ኃይሎች ወደ ሀገር እንዲመለሱ ማድረግና የፖለቲካ ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት የሚያስችል ሁኔታ ፈጥሯል። ይህም የተለያዩ አመለካከቶችን በሰላማዊ ውይይት አስተናግዶ ሀገርን በጋራ የመሥራት ባህልን ለማጠናከር የታለመ ቁርጠኛ እርምጃ ነው።

በተጨማሪም በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 ዓ.ም የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኢትዮጵያ መሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚስተዋሉ ልዩነቶችን በሰላማዊና አካታች ምክክር ለመፍታት ተቋቁሟል። ኮሚሽኑም የአለመግባባትና የልዩነት ምንጮችን በመለየት በሁሉም ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች እና በውጭ በሚኖሩ የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በየምዕራፉ የአጀንዳ ማሰባሰብና የተሳታፊዎች ልየታ አከናውኗል።

ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮም በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ዋናው የምክክር ጉባኤ ለበርካታ ቀናት ተካሂዷል። በዋናው ጉባኤም ከመላ ኢትዮጵያና ከውጭ ሀገራት የተውጣጡ 4 ሺህ የሕዝብ ወኪል ተመካካሪዎች በ10፣ በ50፣ በ250፣ በ500 እና በሥራ ቡድኖች በመደራጀት በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ምክረ ሀሳቦችን ማፍለቅ የቻሉበት ታሪካዊ መድረክ ሆኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት መስከረም 23 ቀን 2019 ዓ.ም በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት ይፋዊ የምክክር ምክረ ሀሳቦች የርክክብ ሥነ-ስርዓት ተካሂዷል። በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተቀመሩ የተመካካሪዎች ምክረ ሀሳቦችንም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ተረክበዋል። የሀገራዊ ምክክሩ ምክረ ሀሳቦች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚስተዋሉ መሰረታዊ ልዩነቶችን በሰላማዊ ምክክር የመፍታት ባህል መገንቢያ ቁልፍ አጀንዳዎች ናቸው።

መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም በተከናወነው ሰባተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ መደበኛ ስብሰባ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን በጠቅላይ ሚኒስትርነት በሰየመበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ የብዝኅ ሥልጣኔ፣ የአስደናቂ ታሪክና እሴቶች ምድር መሆኗን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያውያንን ሕብረ ብሔራዊነት በማጎልበት አለመግባባቶችን በሰለጠነ ምክክር በመፍታት ጠንካራ ሀገረ መንግሥት መገንባት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል። አለመግባባቶችን በጠብመንጃ ለመፍታት መሞከር ጥፋቱ የከፋ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

በዚህም ኢትዮጵያውያን በጋራና በትብብር ችግሮቻቸውን በመቅረፍ የሀገራቸውን ሥልጣኔ ለማረጋገጥ ለአንድ ዓላማ መሥራትና መትጋት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። የምትበለጽግ ብቻ ሳይሆን ዓለምን የምትቀይር የሰለጠነች ኢትዮጵያን መገንባት ለነገ የማይተላለፍ የጋራ የቤት ሥራ መሆኑንም አሳስበዋል።

የመደመር መንግሥት የሕገ-መንግሥትና የአሰራር ማሻሻያ በማድረግ ጭምር የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ምክረ ሀሳቦችን በመተግበር በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባትን ለመገንባት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ከዚህ አንጻር የሽግግር ፍትሕና የዕርቅ ሂደት እንዲሁም ሀገራዊ ምክክር ለዘላቂ ሰላምና ለሀገራዊ መግባባት ወሳኝ መደላድሎች ናቸው። የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የወንጀል ምርመራና ክስ፣ እውነትን መፈለግ፣ ዕርቅ፣ በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ ምህረትና ማካካሻን በማካተት ፍትሕን፣ ተጠያቂነትንና የሕግ የበላይነትን ለማጠናከር ጉልህ ሚና ይጫወታል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ምክረ ሀሳቦችም ለዘመናት የቆዩ የአለመግባባት ችግሮችን በውይይት በመፍታት በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ መግባባትን በመገንባት የመተማመን ባህልን ለማጎልበት የማይተካ ሚና አላቸው።

የመደመር መንግሥት አካታች የፖለቲካ ምኅዳር፣ የሽግግር ፍትሕና ሀገራዊ ምክክር የኢትዮጵያን የቆዩ የአለመግባባት ችግሮች በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ ለመፍታት የተዘረጉ አስፈላጊ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ማዕቀፎች ናቸው። የእነዚህ ሂደቶች ዘላቂ ውጤት በሕዝብ ተሳትፎ፣ በተቋማት ኃላፊነትና በሁሉም ዜጎች መካከል በሚፈጠር መተማመን ላይ ይታነጻል። ይህም ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከርና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በማሳደግ ለሁሉም ዜጎች የሚጠቅም ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና ለመገንባት ወሳኝ ነው።

የኢትዮጵያ ታላቅነት በጥንታዊ ታሪኳ፣ በሥልጣኔዋና በተፈጥሮ ሀብቷ የታነጸ የአብሮነት ማኅተም ነው። የኢትዮጵያውያንን በሕብር የተሸመነ ጸጋ በአንድ የጋራ ሀገራዊ ዓላማ አሰባስቦና አስተባብሮ ማስቀጠልም ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታን በጽኑ አለት ይገነባል። ሀገር በቀል የመግባባት ዴሞክራሲ ግንባታም ወደ ዘላቂ ሰላም፣ የጋራ ብልፅግና እና የሥልጣኔ ከፍታ ያሸጋግራል። ለዚህም ነው በጦር መሣሪያ ከታገዘ ኋላቀር የጉልበት አካሄድ ይልቅ በሐሳብ የበላይነት የተመሰረተ ምክክር የመተማመን ድልድይን በመገንባት የጋራ ሀገራዊ አስተሳሰብ የመቅረጽ ከፍተኛ ኃይል አለው የሚባለው።

ሀገራዊ ምክክር ምክክር ምክረ ሃሳቦችም ልዩነቶችን በጸጋ ተቀብሎ በአብሮነት የመኖር ባህል ማጠናከሪያ መሰረቶች ናቸው። ብዝኅ ድምፅ በነፃነት የሚሰሙበት፣ ቅሬታዎች በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበት፣ ታሪካዊ ቁስሎች በእውነትና በፍትሕ የሚታከሙበት እንዲሁም የጋራ ችግሮች በጋራ የሚቋጩበት ምኅዳር መፍጠር የምክክሩ ማዕከላዊ ዓላማ ነው። የምክክር ሂደቱም በአንድነትና በመከባበር ላይ የተመሰረተ አብሮነትን በማጎልበት፣ የሃሳብ ልዩነቶችን በሥልጡን መንገድ የመፍታት ባህልን ያዳብራል።

የመደመር መንግሥት የፖለቲካ ምኅዳርን የማስፋት፣ የሽግግር ፍትሕን የማጠናከር፣ ዕርቅን የማሳለጥና የሀገራዊ ምክክር ምክረ ሀሳቦችን አሰናስሎ የመተግበር ቁርጠኝነት አለው። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ምክረ ሀሳቦችም በሐሳብ የበላይነት የተመሰረተ ሀገር ግንባታን በማነጽ ሰላማዊ አብሮነትን የሚያጎናጽፍ መሰረት ናቸው።

ሀገር ግንባታ በአንድ ትውልድ ብቻ የሚጠናቀቅ ሥራ ባለመሆኑ ዛሬ የምንመሰርተው የጋራ መግባባት ባህል ለነገው ትውልድ የምናወርሰው ግዙፍ ሀገራዊ እሴት ነው። ትልቅ ሀገር የሚገነባውም ከትልቅ ሕዝብ በሚመነጭ ትልቅ ሐሳብ፣ የጋራ ዓላማና የጋራ ኃላፊነትን በሚጋራ ትውልድ ነው። ኢትዮጵያ የታሪኳን ክብር በሥልጣኔ ከፍታ የሕዝቦቿን ሕብረ ብሔራዊነት ወደ የጋራ ኃይል፣ ሕብረ ብሔራዊነቷንም ወደ የጋራ መፍትሔ እየለወጠች ነው። የምክክር ሂደቱ ምክረ ሀሳቦችም ዘላቂ ሀገር ግንባታን የሚያጎለብቱ ናቸው።

የመግባባት ተራራ በአንድ ሌሊት አይገነባም። በትውልድ ቅብብሎሽ በሥልጡን የዴሞክራሲ መግባባት ባህልና በተቋማት የማስፈጸም ውጤታማነት በሚፈጠር ቀጣይነት ያለው የመተማመን ተግባር እውን ይሆናል። ምክክር የሀገር ሥር ነው፤ መግባባትም የአንድነት ድልድይ ነው። ፍትሕ ደግሞ የዘላቂ ሰላም መሰረት ነው። ኢትዮጵያ በብዝኅነቷ የምትኮራ፣ በአንድነቷ የምትጸና፣ በሥልጣኔዋ የምትበለጽግና በጋራ ርዕይዋ ወደ ታላቅ ከፍታ የምትራመድ ሀገር እንድትሆን የመግባባት ተራራን በጋራ እንገንባ!!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም