ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ የኢኮኖሚ አጋርነታቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ የኢኮኖሚ አጋርነታቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ ለረጅም ጊዜ የቆየውን የኢኮኖሚ አጋርነታቸውን የበለጠ ለማጎልበት እንደሚሰሩ አስታወቁ።
የ2026 የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ በታይላንድ ባንኮክ መካሄዱን ቀጥሏል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የተመራ የኢትዮጵያን ልዑካን ቡድን በስብስባው ላይ እየተሳተፈ ነው።
ልዑካን ቡድኑ ከዓመታዊ ስብሰባው ጎን ለጎን ከፈረንሳይ ግምጃ ቤት ረዳት ዋና ፀሐፊ ቶማስ ሪቪያል ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አካሂዷል።
ይህ ስብሰባ በኢትዮጵያ እና በፈረንሳይ መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ አጋርነት ለመገምገም የሚያስችል መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል።
በውይይቱም ኢትዮጵያ በመተግበር ላይ የምትገኘው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ያመጣው አዎንታዊ ለውጥ እና ፈረንሳይ ለሀገሪቱን የቅድሚያ የልማት አጀንዳዎች እያደረገች የምትገኘው ድጋፍ እና ተሳትፎ ተዳሷል።
በውይይቱ ወቅት ሁለቱ ወገኖች በልማት ፋይናንስ፣ በዘላቂ የብድር ስርዓት እና አስተዳደር፣ በኢንቨስትመንት እንዲሁም በተቋማዊ አቅም ግንባታ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር አጠናክሮ ለማስቀጠል በሚቻልባቸው ዕድሎች ላይ ሀሳቦችን ተለዋውጠዋል።
ውይይቱ የኢኮኖሚ መረጋጋት እና ዘላቂ ዕድገትን ለማረጋገጥ ቀጣይነት ላለው አጋርነት ወሳኝ ሚና እንዳለው አጽንኦት ተሰጥቶታል።