ቀጥታ፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለውጭ አልሚዎች ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3/2019 (ኢዜአ)፦የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መሰማራት ለሚፈለጉ የውጭ አልሚዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የናይጄሪያው ዩናይትድ ካፒታል ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፒተር አሻዴ ገለጹ፡፡ 

የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም የምንዛሬ ክምችት በማሻሻል፣ የመደበኛና ጥቁር ገበያው መካከል ያለውን ልዩነት በማጥበብ የተሳለጠ ግብይት እንዲፈጠር አድርጓል።

የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ፣ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን እና የባንክ ዘርፍ ለውጭ ገበያ ክፍት እንዲሆን በማድረግ ውጤት እያመጣ ነው።

ሪፎርሙ ዓለም አቀፍ ተቋማት ወደ ገበያው እንዲገቡና የፋይናንስ አገልግሎቶችን አስፍቷል፤ በዚህም የናይጄሪያው ዩናይትድ ካፒታል ግሩፕ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ መሰማራት የሚያስችለውን ፈቃድ አግኝቷል።

የዩናይትድ ካፒታል ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፒተር አሻዴ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ መንግሥት በማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ገበያውን ነፃ ለማድረግ የወሰደው እርምጃ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

እርምጃው የሀገሪቱ የገበያ ስርዓት ከመንግሥት ወደ ግሉ ዘርፍ መሪነት የሚያሸጋገር መሆኑን ገልጸው፤ የፋይናነስ ዘርፉ ዕድገትና ሽግግር ለማሳለጥ ወሳኝ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በሪፎርሙ ታግዛ የካፒታል ገበያ ዕውን በማድረግ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ነፃነትና ልማት ሰፊ መድረክ መፍጠሯን ገልጸዋል።

የውጭ ምንዛሪ በገበያ መመራቱ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውን በማቀላጠፍ መሰረታዊ ሽግግር መፍጠር ያስችላልም ብለዋል።

የፖሊሲ ማዕቀፎች ከመንግሥት የትርፍ ክፍያ ወደ ሀገር የመመለስ ዋስትና ጋር ተደራጅተው መቅረባቸው ዓለም አቀፍ አልሚዎች ካፒታላቸውን ለረጅም ጊዜ ስራ ላይ ለማዋል ማረጋገጫ እንደሚሆናቸው ገልጸዋል።

ዩናይትድ ካፒታል ግሩፕ በቅርቡ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ባንክ አገልግሎትና ሌሎችንም የፋይናንስ ዘርፎች መሰማራት የሚችልበትን ፈቃድ ማግኘቱን ገልጸው፤ የዚህ ታሪካዊ የኢኮኖሚ ሽግግር አካል በመሆናችን ኩራት ይሰማናል ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም