የኢትዮጵያ ሜቴዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የሀገሪቱን ልማት የመደገፍ አቅሙን እያሳደገ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሜቴዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የሀገሪቱን ልማት የመደገፍ አቅሙን እያሳደገ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሜቴዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የሀገሪቱን ልማት የመደገፍ አቅሙን እያሳደገ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢንስቲትዩቱን በጎበኙበት ወቅት እንዳሉት፤ እንደ ሜቴዎሮሎጂ ያሉ ተቋማት አቅማቸው መጎልበቱ የአየር ፀባይ ሁኔታ አደጋዎችና ጉዳቶችን አስቀድሞ ለመከላከል ያስችላል።
ድርቅ እና የአየር ንብረት ለውጥን የመሳሰሉ ክስተቶችን አስቀድሞ የመተንበይ አቅም ላይ ክፍተቶች እንደነበሩ አውስተዋል።
መንግስት ባለፉት ዓመታት ባከናወናቸው የሪፎርም ስራዎች ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን በቅድመ-ማስጠንቀቂያ መልክ ማቅረብ መቻሉ፣ አስፈላጊውን ቅድመ-ዝግጅት በማድረግ ሊደርስ ሚችለውን ጉዳቶችን ለመግታት እንዳስቻለ አመልክተዋል።
አስተማማኝ የሜቴዎሮሎጂ መረጃዎችን ወደ ተግባራዊ መመሪያዎች መቀየር የዜጎችን ሕይወት ከማዳን ባለፈ ሀገራዊ ሀብትን የመጠበቅ እና በመረጃ የተደገፈ ውሳኔ የመስጠት አቅምን እንደሚያጎለብትም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።
በተለይም በግብርናው ዘርፍ የሚሰጡ የትንበያ መረጃዎች የእርሻ ጊዜን ለማፋጠን ወይም ለማዘግየት፣ ተስማሚ የዘር ዓይነቶችን ለመምረጥ እና የማዳበሪያ አጠቃቀምን አስቀድሞ ለመወሰን መልካም አጋጣሚ መፍጠራቸውን ተናግረዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ባለፉት ስምንት ዓመታት የተከናወነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከሜቴዎሮሎጂ መረጃዎች ጋር በማቀናጀት በመካሄዱ የተሻለ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።
ችግኞች የንፋስ ግፊትን በመመከት፣ ዝናብ በመሳብ እና የጎርፍ አደጋን በመቀነስ ረገድ የሚጫወቱትን ሚና ተቋሙ ሳይንሳዊ በሆነ ዳታ መደገፉን አመልክተዋል።
የኢንስቲትዩቱ ድጋፍ ለብዙ ዘርፎች ጠቀሜታ ያለውና የውሳኔ መስጠት አቅምና ዝግጁነትን የሚያጠናክር እንደሆነም ነው ያብራሩት።
ዘርፎችን በውጤታማነት ለመምራት አስተማማኝ ዳታ ማግኘት ወሳኝ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የተቋሙን አቅም የበለጠ ማጠናከር ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅት ተቋሙ ከሳተላይት ምልከታ ባሻገር በመላ ሀገሪቱ ባስቀመጣቸው የዳታ ማዕከላት እና የመረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎች አማካይነት መረጃዎችን በወቅቱ በመሰብሰብ፣ በማቀናጀት እና በጥልቀት በመተንተን ለአገልግሎት ማብቃት የሚችልበት አስተማማኝ ደረጃ ላይ መድረሱን አመልክተዋል።
የተቋሙ ስራዎች ብልጽግናን ለማረጋገጥ የተያዘውን ውጥን ለማሳካት ወሳኝ ሚና እንደሚወጣም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ የጎላ እና የሚያኮራ የሜቴዎሮሎጂ አቅም ባለቤት መሆኗን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ወደፊት የራሷን ሳተላይት ተጠቅማ መረጃዎችን በቀጥታ ከሳተላይቱ የምታስተሳስርበትን መንገድ ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።
አንጋፋው ተቋም አሁን ያለበትን ደረጃ ተማሪዎች፣ ተመራማሪዎች እና ወጣቶች እንዲጎበኙና ትምህርት እንዲወስዱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልእክት አስተላልፈዋል።