ቀጥታ፡

ማዕከሉ አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን በማላመድ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየሰራ ነው

አሶሳ፤ ጥቅምት 3/2019 (ኢዜአ)፦የአሶሳ ግብርና ምርምር ማዕከል የአካባቢውን ስነ-ምህዳር የሚላመዱ አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን በማውጣት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማላቅ እየሰራ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ።

የአሶሳ ግብርና ምርምር ማዕከል በኩርሙክ ወረዳ አጉቤላ ቀበሌ እያለማ የሚገኘው የሰሊጥ ሰብል ልማት የመስክ ምልከታ ተካሄዷል።


 

በምልከታው ላይ የተገኙት የቢሮው ኃላፊ አቶ ባበክር ሀሊፋ እንደተናገሩት፤ በክልሉ በምርምር የተረጋገጡ አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ ይገኛል። 

የአሶሳ ግብርና ምርምር ማዕከል በማሽላ፣ በበቆሎ እና በተለያዩ የቅባት እህሎች የሚያወጣቸውን የምርምር ውጤቶች በአሁኑ ሰዓት አርሶ አደሩ በስፋት እየተጠቀመባቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

በኩርሙክ ወረዳ እየለማ የሚገኘው የሰሊጥ ዝርያ ምርትና ምርታማነቱ የተረጋገጠ እንዲሁም የአካባቢውን ሥነ ምሕዳር መላመድ የሚችል መሆኑን በተግባር ያሳየ ነው ብለዋል።

ይህም አርሶ አደሩ በግብርና ሥራ ተሳታፊ እንዲሆንና በክልሉ የቅባት እህሎችን ምርታማነት ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።


 

የአሶሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ደስታ በቀለ በበኩላቸው፤ ማዕከሉ በየጊዜው የሚያወጣቸው የምርምር ሥራዎች ከምርታማነታቸው በተጨማሪ የአርሶ አደሩን ጉልበት እና ወጪ የሚቆጥቡ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

በኩርሙክ ወረዳ እየለማ የሚገኘው የሰሊጥ ሰብል ቁመና በቀጣይ አርሶ አደሩ በስፋት እንዲያለማ የሚያደርግና ተባይን መቋቋም የሚችል መሆኑንም አስረድተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም