በከተሞች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ማህበረሰቦችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት ተመዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
በከተሞች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ማህበረሰቦችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት ተመዝግቧል
አርባምንጭ፣ ጥቅምት 3/2019 (ኢዜአ)፡-በከተሞች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ማህበረሰቦችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት መመዝገቡ ተገለጸ።
በአርባምንጭ ከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔትና ስራ ፕሮጀክት የተካሄደ የአሰፋ ጨቦ መታሰቢያ ሙሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስፋፊያ ግንባታ ተጠናቆ ዛሬ ተመርቋል።
በስነ ስርአቱ ላይ የተገኙት የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት እና ሥራ ፕሮጀክት አስተባባሪ አንዷለም ገሠሠ እንደገለጹት በሀገሪቱ በ88 ከተሞች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ማህበረሰቦችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት ተመዝግቧል።
በዚሁ መሠረት ባለፉት አምስት ዓመታት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዜጎችን በትምህርት፣ በጤናና በሌሎችም የልማት ዘርፎች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል።
የአርባምንጭ ከተማ የአሰፋ ጨቦ መታሰቢያ ሙሉ አንደኛ ትምህርት ቤት ማስፋፊያ ግንባታም የዚሁ አንድ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ወገኖችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ሃላፊ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ በበኩላቸው የአሰፋ ጨቦ መታሰቢያ ሙሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስፋፊያ ግንባታ በቢሮውና በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ትብብር የተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል ።
ትምህርት ለሀገር ዕድገትና ብልጽግና ጉልህ ፋይዳ ያለው በመሆኑ የተገነባው ትምህርት ቤት በዕውቀት የታነጸ ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት አስተዋጽኦው የላቀ ነው ብለዋል።
የትምህርት ተደራሽነት ለማስፋፋትና ጥራቱን ለማረጋገጥ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ለትምህርት ልማት ስራ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል ።
የአርባምንጭ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ሊዲያ ከንቲባ በበኩላቸው የትምህርት ቤቱ ማስፋፊያ ግንባታ ብቁ ዜጎችን ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ብለዋል።
ትምህርት ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዕድገት ጉልህ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ከተማ አስተዳደሩ ዜጎች ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
በከተማው የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን በቤተ ሙከራና በቤተመጻሕፍት እንዲሁም በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲታገዙ በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።