የቴክኒክና ሙያ መምህራንና ተቋማት መካከለኛ የሰው ኃይል በማፍራት ላይ ማተኮር አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የቴክኒክና ሙያ መምህራንና ተቋማት መካከለኛ የሰው ኃይል በማፍራት ላይ ማተኮር አለባቸው
ጎንደር፣ ጥቅምት 3/2019 (ኢዜአ)፡-የቴክኒክና ሙያ መምህራንና ተቋማት መካከለኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት የጀመሩትን ተግባር አጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው የጎንደር ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።
የክልሉ ስራና ክህሎት ቢሮ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና ከኢንተርፕረነር ሺፕ ዲቨሎፕመንት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የአሰልጣኞች ስልጠና በጎንደር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ መሰጠት ጀምሯል።
የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ደብሬ የኋላ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገትን ለማፋጠን መካከለኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ሃይል በማፍራት ስራ ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል።
ለዚህም የቴክኒክና ሙያ መምህራንና ተቋማት አዲሱን የስልጠናና ስርዓተ ትምህርት በተግባር በመተርጎም ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ወጣቱን ትውልድ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በዕውቀትና ክህሎት በማነጽ የስራ እድል ፈጣሪና ተጠቃሚ እንዲሆን የመምህራን የስራ ተነሳሽነትና ርብርብ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል ብለዋል።
ፈጣን ሀገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ የሚቻለው የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ላይ አተኩሮ በመስራት መሆኑን ጠቁመው አስተዳደሩም ለዘርፉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የጎንደር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ተስፋሁን መኮንን በበኩላቸው፤ ስልጠናው በአዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ በጎንደር ቀጠና የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችን ለማብቃት ያለመ ነው።
ለ10 ቀናት በሚቆየው ስልጠናም ፖሊሲውን በማሳወቅ፣ ሙያን ወደ ቢዝነስ በመቀየር፣ በመደራጀት አብሮ የመስራት ስነ-ምግባርና ሌሎች ጉዳዮች ላይ በማተኮር ይሰጣል ብለዋል።
ስልጠናው የተግባቦት፣ የቡድን ስራ፣ የጊዜ አጠቃቀም፣ የችግር አፈታትና የውሳኔ ሰጪነት ክህሎቶችን ለማዳበር ያስችላል ያሉት ደግሞ ስልጠናውን በመስጠት ላይ የነበሩት አቶ ጌታቸው አለባቸው ናቸው።
ከሰልጣኞቹ መካከል መምህር ባዬ ከበደ፤ ስልጠናውን ከጨረሱ በኋላ የአሰልጣኝነት ሚናቸውን በአግባቡ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ተመሳሳይ ስልጠናዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ በሐሮማያ እና ሐዋሳ እየተሰጠ መሆኑም በዚሁ ወቅት ለማወቅ ተችሏል፡፡