ጅማ ዩኒቨርሲቲ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ተቋማዊ ብቃቱን ለማሳደግ በቅንጅት እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ጅማ ዩኒቨርሲቲ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ተቋማዊ ብቃቱን ለማሳደግ በቅንጅት እየሰራ ነው
ጅማ፣ ጥቅምት 3/2019 (ኢዜአ)፡- ጅማ ዩኒቨርሲቲ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለውን ተቋማዊ ብቃትና የተማሪዎች ክህሎት ለማሳደግ በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገለጸ።
ዩኒቨርሲቲው ከአፍሪካን ዲጂታል ኢኖቬሽን ኤንድ ቴክኖሎጂ አካዳሚ ጋር በቴክኖሎጂ ልማት፣ በስልጠናና በሙያ ምክር አገልግሎት ዘርፎች በጋራ ለመስራት ዛሬ ስምምነት አድርጓል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሰው ሰራሽ አስተውሎትን ለመማር ማስተማርና ለምርምር ለማዋል አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዩች ዙሪያ ለዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ባለሙያዎች ስልጠና ተሰጥቷል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ደረጀ እንግዳ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ለማስፋፋት ከተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ ነው።
ዩኒቨርሲቲው ሰራተኞችን በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ብቁ ከማድረግ ባሻገር በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ የተካኑ ዜጎችን ለማፍራት እየሰራ መሆኑንም አክለዋል።
በተለይም በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ለጥሩ ዓላማ የመጠቀም ልምድ እንዲዳብር ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብና ለሌሎች ተጠቃሚዎች ስልጠናዎችን ተደራሽ የማድረግ ስራን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ የአይሲቲ ማዕከል ዳይሬክተር መሀመድ ሙንታዝ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት፤ አካዳሚው በዩኒቨርሲቲው እየሰጠ ያለው ስልጠና በቀጣይ የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀምን ለማሳደግ ጉልህ ሚና አለው።
የአፍሪካን ዲጂታል ኢኖቬሽን ኤንድ ቴክኖሎጂ አካዳሚ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፕሮፌሰር ሸጋው አናጋው በበኩላቸው፣ አካዳሚው ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በቴክኖሎጂ ልማት፣ በስልጠናና በማማከር ላይ ለመስራት መስማማቱን ገልጸዋል።
ስምምነቱ ዩኒቨርሲቲዎች የሰው ሰራሽ አስተውሎትን ለመማር ማስተማርና ለምርምር በአግባቡ እንዲጠቀሙ ለማገዝ ያለመ መሆኑንም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ዘርፍ፣ በተለይም በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ አበረታች ለውጦችን እያስመዘገበች መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩት መቋቋሙና ለዘርፉ የሚያግዝ ፖሊሲ መውጣቱ የቴክኖሎጂ ልማቱን ለማሳለጥ የሚያስችሉ አስፈላጊ እርምጃዎች ናቸው ብለዋል።
ስልጠናው ለሁለት ቀናት የሚሰጥ መሆኑም ተመላክቷል።