ቀጥታ፡

የሃይማኖት ተቋማት ለሀገር ግንባታና ለሕዝቦች አብሮነት ታላቅ ሀገራዊ ኃይል ናቸው 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3 /2019 (ኢዜአ)፦የሃይማኖት ተቋማት ለሀገር ግንባታ፣ ለሕዝቦች አብሮነት እንዲሁም አንድነት ታላቅ አቅም መሆናቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት 45ኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መካሄድ ጀምሯል፡፡ 


 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሀገሪቱ ታሪክ፣ ባህል፣ ሥነ-ጽሑፍ፣ ቅርሶችና የምኅንድስና ጥበባት ግንባታ ታሪካዊና ዘላቂ ሚና አበርክታለች።

ቤተ ክርስቲያኗ ለዘመናት የትምህርት፣ የቋንቋና የሥነ-ጽሑፍ ማዕከል ሆና በማገልገል ለሀገር ነፃነትና ለሕዝቦች አብሮነት ፈር ቀዳጅ ሆና መዝለቋንም አብራርተዋል።

አባቶች፣ እናቶች በነበራቸው ጽኑ መንፈሳዊ ተጋድሎና እምነት ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን ዘላቂ አሻራ ማኖራቸውን በማስታወስ፣ የአሁኑ ትውልድም ይህንን አርዓያነት በመከተል ሀገራዊ ችግሮችን በመፍታት ረገድ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚገኙ ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት በጋራ የሚያስተሳስራቸው ዋና መሠረት ኢትዮጵያዊነት መሆኑን አስገንዝበዋል።


 

የሃይማኖት ተቋማት የሀገር ግንባታና የሰላም መሠረት መሆናቸውን በመግለጽ፤ ይህን አበርክቷቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

መንፈሳዊ አባቶች፣ ካህናት፣ ሊቃውንትና ምዕመናን የተሰጣቸውን አደራ በመወጣት ዘላቂ ሰላምን በማጽናት፣ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር፣ ድህነትና ኋላቀርነትን በማስወገድ በኩል አዎንታዊ ሚናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ፤ ሰበካ ጉባዔው በይፋ መጀመሩን አብስረዋል፡፡

የጉባኤው ዋነኛ ዓላማ ፍቅርን በማስፈን፣ አብሮነትን ለማጠናከር እና ተግቶ ለመስራት ቁርጠኝነት የሚታደስበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ እና የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በዚሁ ወቅት፤ ሰበካ ጉባዔው የ2018 ዓ.ም አጠቃላይ የስራ አፈጻጸም ገምግሞ የ2019 ዓ.ም የስራ አቅጣጫ ያስቀምጣል ብለዋል።

የምዕመናንን የአገልግሎት ፍላጎት ለማሟላት እንዲሁም በኢኮኖሚ የበለጸገችና የተጠናከረች ተቋም ለመገንባት የሚያስችል ሥርዓት ተዘርግቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው በቤተ-ክህነት ደረጃ የተለያዩ የልማትና የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን አመላክተዋል።

የሰበካ ጉባኤ አስተዳደር ሲስተም፣ የሰው ኃይል አስተዳደር ሲስተም እና የድረ ገጽ መግቢያ ፓርታል ተጠናቅቀው ተመርቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም