ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ ለኃይል ሴክተር ሪፎርም ኢንቨስትመንትና ማዘመኛ ምዕራፍ አንድ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል የብድር ስምምነትን አፀደቀ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3/2019 (ኢዜአ)፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለኃይል ሴክተር ሪፎርም ኢንቨስትመንትና ማዘመኛ ምዕራፍ አንድ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል የ145 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ብድር ስምምነትን በሙሉ ድምጽ አፅድቋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ አከናውኗል።


 

ምክር ቤቱ በስብስባው በመንግሥት እና በዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር መካከል ለኃይል ሴክተር ሪፎርም ኢንቨስትመንትና ማዘመኛ ምዕራፍ አንድ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል የ145.8 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ አፅድቋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ፍቃዱ ተሰማ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ማብራሪያ ፤ የብድሩ ዓላማ የአዲስ አበባን የኃይል ማስተላለፊያ መረብ ለማጠናከር፣ አዳዲስ የኃይል ጣቢያዎችን መገንባትና ነባሮቹን ማሻሻል እንዲሁም የመሬት ውስጥ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን መዘርጋት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለምታስተናግደው 32ኛው የተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP 32) አስተማማኝና ዘመናዊ የኃይል አቅርቦትን ለማረጋገጥ የብድር ስምምነቱ ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

ብድሩ ቀላልና አነስተኛ የገንዘብ ጫና የሚፈጥር ተብሎ የተገለጸ ሲሆን የስድስት ዓመት የእፎይታ ጊዜን ጨምሮ በ 31 ዓመታት ውስጥ ተከፍሎ የሚጠናቀቅ መሆኑ ተብራርቷል።

የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትሩ አያይዘውም ብድሩ ከሀገሪቱ የብድር አሰጣጥና አስተዳደር ስትራቴጂ ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጣጣምና ለዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑን አመልክተዋል።

ምክር ቤቱ በመንግሥት እና በዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር መካከል ለኃይል ዘርፍ ማሻሻያ፣ ኢንቨስትመንትና ማዘመኛ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የተፈረመውን የ145.8 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተጨማሪ ቀላል የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅን፤ አዋጅ ቁጥር 1441/2019 አድርጎ በሙሉ ድምፅ አጽድቆታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም