በኢትዮጵያ መድህን ተቆጣጣሪ ኮሚሽን ማቋቋም የሚያስችል አዲስ አዋጅ እየተዘጋጀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ መድህን ተቆጣጣሪ ኮሚሽን ማቋቋም የሚያስችል አዲስ አዋጅ እየተዘጋጀ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3 /2019 (ኢዜአ)፦የመድህን አገልግሎት ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ የኢትዮጵያ መድህን ተቆጣጣሪ ኮሚሽን ማቋቋም የሚያስችል አዲስ አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የቁጥጥር ዳይሬክተር በላይ ቱሉ ለኢዜአ እንዳሉት፤ አዲሱ የመድህን አዋጅ ከሚኒስትሮች ምክር ቤት አልፎ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተልኳል።
በኢትዮጵያ የመድህን አገልግሎት ባለፉት 30 ዓመታት ዕድገት እያሳየ ቢሆንም ከሀገሪቱ አቅምና ከዓለም አቀፍ ደረጃ አንፃር ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
የመድህን አገልግሎት ዕድገት የሚለካው ለኢኮኖሚው በሚያበረክተው አስተዋጽኦ፣ የመድህን አገልግሎት ተጠቃሚዎች ብዛት እና በአገልግሎቶቹ አይነት መሆኑን ገልጸው፤ በሁሉም መለኪያዎች አነስተኛ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ካላት የኢኮኖሚ አቅም፣ መድህን የመግዛት ፍላጎት ካለው ህዝብ ቁጥርና ተመሳሳይ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት አንፃር ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
የመድህን አገልግሎት ለጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት የሚያበረክተው በዓለም 6 ነጥብ 5 በመቶ፣ በአፍሪካ 3 ነጥብ 6 በመቶ እንዲሁም በሰብ-ሰሃራን አፍሪካ 2 ነጥብ 9 በመቶ ድርሻ እንዳለው ገልጸው፤ በኢትዮጵያ 0 ነጥብ 3 በመቶ አስተዋጽኦ በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
የመድህን ዘርፉ ለውጭ ገበያ ዝግ ሆኖ መቆየቱ፣ ዘርፉን መቆጣጠር፣ ማሳደግና መምራት የሚችል ኮሚሽን ማቋቋም አስፈላጊ በመሆኑ አዋጁን ለማውጣት ገፊ ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥና ተደራሽነትን ለማሻሻል በሰው ሀይልና በቴክኖሎጂ ማዘመን እንደሚገባ ገልጸው፤ ያላትን ዕምቅ አቅም ጥቅም ላይ ማዋል ያስችላል ብለዋል።
በተመሳሳይ ስራ የተለየ ውጤት መጠበቅ እንደማይቻል ገልጸው፤ የህይወት መድህን ከጠቅላላ የመድህን አገልግሎት እንዲያድግ ማድረግ የሚያስችል አሰራር ይፈጥራል ብለዋል።
በአፍሪካ የመድህን አገልግሎትን በማዕከላዊ ባንኮች የሚቆጣጠሩት ኢትዮጵያን ጨምሮ 6 ሀገራት ብቻ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ሌሎች ራሱን የቻለ የመድህን ተቆጣጣሪ ባለስልጣን አልያም ከጡረታ ተቋም ጋር ተቀናጅቶ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ለዚህም በኢትዮጵያ የመድህን አገልግሎት ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ የመድህን ተቆጣጣሪ ኮሚሽን ማቋቋም የሚያስችል አዲስ አዋጅ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ በአዋጁ መሰረት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሲሰጥ የነበረውን አገልግሎት ከተጨማሪ ሀላፊነት ጋር ይዞ በገለልተኝነት ይቋቋማል ብለዋል።
አዲሱ የመድህን አዋጅ ከሚኒስትሮች ምክር ቤት አልፎ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተልኳል ያሉት አቶ በላይ፤ ለመድህን ተቋማት ዕድገት በትጋት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በመሆኑም ለመድህን ተቋማት ፈቃድ ይሰጣል፤ ውጤታማነታቸውንም ይቆጣጠራል፣ ለኢንዱስትሪው ዕድገት በሚበጅ መንገድ እንዲመሩ ጤናማነታቸውን ይቆጣጠራል ብለዋል።
የመድህን አዋጁ ከማክሮ ኢኮኖሚ፣ ከቁጥጥር ስርዓቱ እና ከገበያው የሚመነጩ የዘርፉን ችግሮች መፍታት እንዲችል ተደርጎ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
የሕይወት ኢንሹራንስ የሀገራትን የኢኮኖሚ ዕድገትና የዜጎችን የኢኮኖሚ ደረጃ ማሳያ መሆኑን ገልጸው፤ በኢትዮጵያ ገና በመነሳት ላይ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የንብረት ኢንሹራንስ 94 በመቶ ድርሻውን መያዙን በመጥቀስ፤ የሕይወት ኢንሹራንስ ቢያንስ 40 በመቶ መድረስ እንዳለበት ገልጸዋል።
በአጠቃላይ የመድህን ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ዋጋ በመቀነስ ላይ ከተመሰረተ ውድድር ወደ አገልግሎት ጥራትና አይነት ማተኮር ይገባል፤ አዋጁ ለዚህም አጋዥ ይሆናል ብለዋል።