የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጠንካራ አጋርነት የሚጠይቅ በመሆኑ የድርሻችንን እየተወጣን ነው - ኢዜአ አማርኛ
የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጠንካራ አጋርነት የሚጠይቅ በመሆኑ የድርሻችንን እየተወጣን ነው
ሰመራ፤ ጥቅምት 3 /2019 (ኢዜአ)፦የባህር በር ባለቤትነትን የማረጋገጥ ጉዳይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጠንካራ አጋርነት የሚጠይቅ በመሆኑ የድርሻችንን እየተወጣን ነው ሲሉ በአፋር ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።
ኢትዮጵያ ከባህር በር እንድትርቅ የተደረገበት ታሪካዊ ሂደት ሕጋዊ መሠረት የሌለውና የኢትዮጵያ የባህር በር ማጣት ለንግድ ሚዛን መዛባትና በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ከባድ ጫና መፍጠሩን ያነሱት ፓርቲዎቹ፣ ችግሩን በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ ጥረት ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል።
የባህር በር ባለቤትነትን የማረጋገጥ ጉዳይ የዜጎችን ንቁ ተሳትፎና ይበልጥም የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጠንካራ አጋርነት የሚጠይቅ በመሆኑ የድርሻቸውን እየተወጡ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
ይህ ጥረት ልዩነት የሌለበት አገራዊ አጀንዳ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር (አርዱፍ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ መሐመድ አወል ወግሪስ፤ ኢትዮጵያን ከባህር በር እንድትርቅ ለማድረግ የተሄደበት መንገድ ሕጋዊ መሠረት የሌለውና ታሪካዊ ፍትሐዊነትን የካደ በመሆኑ፣ ይህንን ታሪካዊ ስህተት በማረም ሂደቱን ለማሳካት እንታገላለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር መኖር ቀጠናዊ ተደማጭነቷን ከፍ ለማድረግና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ከፍተኛ አቅም ያለው መሆኑን በመጠቆም፤ ይህንን ለማሳካት የተሄደበት የ"ሰጥቶ መቀበል" የዲፕሎማሲ መርህ ሙሉ በሙሉ የሚደገፍና ብልህነት የተሞላበት መሆኑንም አብራርተዋል።
የአፋር ነፃ አውጪ ግንባር ፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የገቢ ረሱ ዞን አስተባባሪ አቶ መሐመድ ኢስማኤል በበኩላቸው፤ ከባህር በር መራቃችን ያስከተለውን ኢኮኖሚያዊና ስትራቴጂካዊ ጉዳት በመረዳት፣ ለሀገራችን የባህር በር ባለቤትነት መረጋገጥ የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለቀይ ባህር ቅርብ በሆነ ስትራቴጂካዊ ርቀት ላይ ብትገኝም፣ ለዓመታት ተነጥላና ተገልላ መቆየቷ ፍጹም አግባብነት የሌለውና የታሪክ ስህተት እንደነበር አቶ መሐመድ ገልጸዋል።
ይህንን ብሔራዊ ጉዳይ ለመፍታት እየተሄደበት ያለው ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ እጅግ የሚደነቅ በመሆኑ ፓርቲያቸው ከምንጊዜውም በላይ ለስኬታማነቱ በንቃት እንደሚሠራ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት መረጋገጥ ሀገሪቱ በየዓመቱ ለወደብ ኪራይና ለሎጂስቲክስ አገልግሎት ክፍያዎች የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ በቀጥታ ለአገር ውስጥ ልማት ለማዋል ያስችላል ብለዋል።