ቀጥታ፡

በሲዳማ ክልል የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ ቅንጅታዊ ስራዎች ይጠናከራሉ

ሀዋሳ፤ ጥቅምት 3 /2019 (ኢዜአ)፦በሲዳማ ክልል የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ ቅንጅታዊ ሥራዎች እንደሚጠናከሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር መሳይ ሃይሉ (ዶ/ር) ገለጹ።

የመደመር መንግስት ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የውይይት መድረክ በሃዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር መሳይ ሀይሉ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ የክልሉ መንግስት የህዝብን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነትን ይበልጥ ለማረጋገጥ ህዝብን በማሳተፍ በተደመረ አቅም ይሰራል።

በተለይ የህዝብ የልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት በአጭርና በረዥም ጊዜ የሚከናወኑትን ለይቶ ወደሥራ እንደሚገባ ገልጸው፣  ፈጣን ምላሽ ለሚፈልጉት ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ለመስጠት በርብርብ ይሰራል ብለዋል።  

የክልሉ መንግስት በሚያከናውናቸው የልማት ሥራዎች ህዝቡ የሚያደርገው ተሳትፎና ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመልክተዋል።  

በክልሉ መልካም አስተዳደርን ማስፈንና የልማት ፀጋዎችን በአግባቡ ለይቶ መጠቀም ሌላው የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም ርዕስ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።

መንግስት ባለፉት ዓመታት ባከናወናቸው ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች የህዝቡ ኑሮ እየተሻሻለ ከመምጣቱ ባለፈ የክልሉን የብልጽግና ጉዞ ለማፋጠን እያገዘ መሆኑንም አስታውቀዋል። 


 

በቀጣይም የክልሉን ህዝብ የልማት ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ ጠንካራ ተቋማትን ከመገንባት ባለፈ አገልግሎት አሰጣጡን የማዘመን ሥራ ትኩረት እንደተሰጠውም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

የወጣቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን ጨምሮ በክልሉ የልማት ሥራዎች በቅንጅት እንደሚከናወኑም ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል።

የዛሬው የውይይት መድረክ ዓላማም በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ የጋራ መግባባት መፍጠርና ከህብረተሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለይቶ ምላሽ ለመስጠት ያለመ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በመድረኩ ላይ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም የተቋማት ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም