ቀጥታ፡

የጣና ፎረም ታዳሚዎችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጅት ተደርጓል

ባህርዳር፤ ጥቅምት 3 /2019 (ኢዜአ)፦  በባህር ዳር ከተማ የሚካሄደው የጣና ፎረም ታዳሚዎችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጅት መደረጉን  የአማራ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው  ፎረሙን ለማዘጋጀት እየተደረገ ባለው ዝግጅትና የኮሙኒኬሽን ስራዎች ላይ በማተኮር ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አባይ መንግስቴ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ከጥቅምት 13 እስከ 15 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ በባህርዳር ከተማ የሚካሔደው የጣና  ፎረምን ስኬታማ በሆነ መንገድ ለማጠናቀቅ የተሟላ ዝግጅት ተደርጓል።

ፎረሙ የኢትዮጵያን ገጽታ በሚገነባና እድገቷን አጉልቶ በሚያሳይ መልኩ የሚካሔድ መሆኑን ተናግረዋል።

የጣና  ፎረም አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው ጥበብና አመራር ለመፍታት የሚካሄድ መሆኑንም አክለዋል።

በባህርዳር ከተማ እስካሁን የተካሄዱ 11 የፎረሙ ስብሰባዎችም በአህጉሩ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመለየት ለመሪዎች ጉባኤ የመፍትሄ ሃሳብ በማቅረብ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም በአፍሪካ ሰላምና መረጋጋትን በማስፈን  እድገትና ልማትን በማፋጠን ላይ በመምከር የመፍትሄ ሃሳቦችንና የቀጣይ እቅጣጫዎች  እንዲመነጩ መደረጉን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም አፍሪካ ያላትን ሃብት ተጠቅማ እንዳትለማ እንቅፋት በሆኑ ህገ- ወጥ የሰዎችና የገንዘብ ዝውውር ላይ በመወያየት ችግሩ የሚፈታበትን መንገድ ማመላከት እንደተቻለ አመልክተዋል።

“በአፍሪካ የሰላም መንገዶች፣ የኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትና የጂኦፖለቲካ ለውጥ”  በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደውን የዘንድሮው የ12ኛው የጣና ፎረም በአፍሪካ ሰላም፣ መረጋጋትና እድገት ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ለመላው የጥቁር ህዝቦች ነጻነት እንደታገለችው ሁሉ ዛሬም የራሷን ልማትና እድገት በማረጋገጥ ወደ አህጉሩ አባል ሀገራት እንዲስፋፋ የበኩሏን ኃላፊነት እየተወጣች እንደምትገኝ አስረድተዋል።

በባህርዳር ከተማ የሚገኙ ሆቴሎችና ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ተቋማትም ለፎረሙ የሚመጡ የአፍሪካ መሪዎችን እንዲሁም  ከፍተኛ ተመራማሪዎችና ባለሙያዎችን  ለማስተናገድ የሚያስችል ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

12ኛው የጣና ፎረም በባህርዳር ከተማ ከጥቅምት 13 እስከ 15 ቀን 2019 ዓ.ም ይካሄዳል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም