ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ለሀገሪቱ ልማትና አቅም ወሳኝ ሥራዎችን የሚያከናውን የረጅም ዘመን እድሜ ያለው ተቋም ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3 /2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የተሟላ የአየር ትንበያ አገልግሎት በመስጠት ለሀገሪቱ ልማትና አቅም ወሳኝ ሥራዎችን የሚያከናውን የረጅም ዘመን እድሜ ያለው ተቋም ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩትን ጎብኝተዋል፡፡

ጉብኝታቸውን አስመልክተው በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ተቋሙ የተሟላ የአየር ትንበያ አገልግሎት በመስጠት ለሀገሪቱ ልማትና አቅም ወሳኝ ሥራዎችን የሚያከናውን የረጅም ዘመን እድሜ ያለው ተቋም ነው ብለዋል።


 

‎ጉብኝቱ እየተለዋወጠ ያለውን የአየር ፀባይና የአየር ንብረት ሁኔታዎችን ለመረዳት እና ምላሽ ለመስጠት ያለንን አቅም ለማጠናከር ሚቲዎሮሎጂያዊ መረጃዎችን የመሰብሰብ፣ የሳይንሳዊ ምርምር እና የቴክኖሎጂ ዕድገት ያለውን የላቀ ጠቀሜታ ያረጋገጠ ሆኖ አግኝቸዋለሁ ሲሉም ገልጸዋል።

‎‎እንደ ኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ያሉ ተቋማትን ማጠናከር እጅግ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ግብርና፣ ውሃ፣ ጤና፣ አቪዬሽን እና የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራርን ጨምሮ ቁልፍ ዘርፎች የሚደገፉባቸውን አገልግሎቶች ለማሻሻል በሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እና በመረጃ መሠረተ-ልማት ላይ መዋዕለ-ንዋይ ማፍሰስ ወሳኝ ነውም ብለዋል።


 

በተለይም አደጋዎችን አስቀድሞ ለመተንበይ፣ የትኞቹ አካባቢዎች ላይ ጣልቃ ገብነት ይበልጥ እንደሚያስፈልግ ለመወሰን፣ እንዲሁም ወቅታዊና ውጤታማ በሆነ መንገድ እንድንንቀሳቀስ ለማድረግ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶች ያላቸው ጠቀሜታ አበረታቶኛል ሲሉም ገልጸዋል።

አስተማማኝ መረጃ ወደ ተግባራዊ መመሪያዎች ሲቀየር ሕይወትን ይታደጋል፣ ሐብትን ይጠብቃል፣ እንዲሁም የተሻለ ውሳኔ ለመስጠት ያግዛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም