ቀጥታ፡

ቡና እና ኦቾሎኒን ዕሴት ጨምረው በማቀነባበር ውጤታማ የሆኑ የጅማ ወጣቶች

ጅማ ፤ ጥቅምት 3 /2019 (ኢዜአ)፦ በጅማ ከተማ የሚገኙ ወጣቶች ቡናና ኦቾሎኒን ዕሴት ጨምረው በማቀነባበር ለራሳቸውና ለሌሎች የገቢ ምንጭ መፍጠራቸውን ገለጹ።

የጅማ ዞንና አካባቢው በከፍተኛ የቡናና የኦቾሎኒ ምርት የታወቀ ቢሆንም፣ ምርቶቹ በአብዛኛው ያለተጨማሪ ማቀነባበር በጥሬው ወደ ገበያ የሚቀርቡ በመሆናቸው ከአምራቹ እስከ ወጣቱ ተጠቃሚ የሚሆነው አነስተኛ  ነበር። 

ከዚህ ባለፈም በአካባቢው የሚገኙ በርካታ ወጣቶች በቂ የሥራ ዕድል ባለመኖሩ ምክንያት ለሥራ አጥነት ተጋልጠው ቆይተዋል።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአነስተኛና ጥቃቅን ማህበራት የተደራጁ የጅማ ከተማ ወጣቶች ይህንን ክፍተት ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር ላይ ይገኛሉ። 


 

ወጣቶቹ ጥሬ ምርቶችን በቀጥታ ከመሸጥ ይልቅ በቴክኖሎጂና በፈጠራ ታግዘው የቆሎ፣ የኦቾሎኒ ቅቤ፣ የታሸገ ዱቄትና የታሸጉ የቡና ምርቶችን በጥራት በማቀነባበር ለገበያ ማቅረብ ጀምረዋል። 

ይህም በአካባቢው የሚመረቱ የግብርና ምርቶችን ዕሴት ከመጨመሩም በላይ፣ የወጣቶቹን ገቢ በማሳደግና ለሌሎችም የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

የጅማ ከተማ ነዋሪ ወጣት ጁኔዲ አሊ በሥራ አጥነት ምክንያት ጊዜው ይባክን እንደነበር ይናገራል። 


 

ከጊዜ በኋላ ግን አካባቢውን በመቃኘትና ጥናት በማድረግ የተፈጨ ቡናን በጥራት ለማቅረብ በማቀድ ከጓደኞቹ ጋር ተደራጅቶ ወደ ሥራ መግባቱን ገልጿል።

ለሥራው አስፈላጊውን ሙያዊ ሥልጠና ከማግኘት ጀምሮ ክትትልና ድጋፍ ከከተማ አስተዳደሩ እንደተደረገለት የገለጸው ወጣቱ፣ በአሁኑ ወቅት ቡናን በማቀነባበር በጥራት ለገበያ እያቀረበ መሆኑን ተናግሯል።

ወጣቱ ጥሩ የገበያ ትስስር ማግኘቱን በመግለጽ፣ ከራሱና ከጓደኞቹ ባሻገር ለሌሎችም የሥራ ዕድል መፍጠሩን አስረድቷል።

ሌላኛው ወጣት ነጃ ደኑር ከጓደኞቹ ጋር በመደራጀት ኦቾሎኒን ወደ ኦቾሎኒ ቅቤ በማቀነባበር የራሳቸውን የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።

የማሽን ግዢና የመሥሪያ ቦታ ሁኔታ ከተመቻቸላቸው በኋላ ወደ ሥራ የገቡት ወጣቶቹ፣ በተለይም ለ13 የአካባቢው እናቶች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።

ወጣቶቹ የሚያመርቱትን የኦቾሎኒ ቅቤ ለሱቆችና ለካፌዎች እንደሚያቀርቡ የገለጸው ወጣት ነጃ፤ በቀጣይ ምርታቸውን በማስፋፋት ወደ ኢንቨስትመንት ደረጃ የማሸጋገር ፍላጎት እንዳላቸው ተናግሯል።

ከምርቱ ጋር በተያያዘ የጥራት ምርመራ መደረጉን ገልፆ፣ ይህም ምርቱን ለገበያ በሚያቀርቡበት ሂደት ዉስጥ እገዛ እንዳደረገላቸው አክሏል።

 ወይዘሮ ፎዜ አባፊራ የሥራ ዕድል ማግኘታቸው ደስታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል። 


 

በተመሳሳይ ወይዘሮ ወዚፋ አባራያና ሸምሴ አባሞጋም ከሥራ ዕድሉ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በጅማ ከተማ የሥራ ዕድል ፈጠራ ጽሕፈት ቤት የሥራ ዕድል ፈጠራ ቡድን መሪ አቶ አሸናፊ ግርማ፣ በዘንድሮው ዓመት ለ31 ሺህ 700 ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱንና በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለ2 ሺህ 300 ዜጎች የዕድሉ ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ወጣቶችን በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎትና በግብርና ዘርፎች ለማሰማራት እየተሠራ መሆኑን የገለጹት አቶ አሸናፊ፣ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ብቻ ከ7 ሺህ 400 በላይ ዜጎችን በዓመቱ ለማሰማራት መታቀዱን አስረድተዋል።


 

በጎጆ ኢንዱስትሪም በ11 ዓይነት ዘርፎች ወጣቶችን በማደራጀት ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ ሲሆን፣ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ብቻ 23 ማኅበራት ተደራጅተው በዘርፉ  ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ከእነዚህ ማኅበራት መካከል ኦቾሎኒን ወደ ኦቾሎኒ ቅቤ በማቀነባበር ለገበያ የሚያቀርቡ ሁለት ማኅበራትና ቡናን በማቀነባበር በጥራት የሚያቀርቡ ማኅበራት እንደሚገኙበትም አክለዋል።

ሥራ ለጀመሩት ወጣቶች ምርታቸውን ለገበያ እንዲያቀርቡ በተለያዩ ባዛሮችና በሌሎች አማራጮች ቅድሚያ በመስጠት የገበያ ትስስር እየተፈጠረ መሆኑንም አቶ አሸናፊ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ምርቶቹ የጥራት ደረጃቸውን እንዲጠብቁ ከመድኃኒትና ምግብ ቁጥጥር ባለሥልጣን ጋር በቅንጅት የክትትል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቀጣይም ወጣቶች የሥራ ዕድላቸውን አስፋፍተው የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የብድርና የገበያ ትስስር አማራጮችን ለማመቻቸት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም